“ሀገር ችግር ውስጥ ስትገባ እኛም ችግር ላይ መውደቃችን ነው””በሁለም መስክ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ ዝግጁ ነን”
ይህን የተናገሩት የገነት ሆቴልና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሰራተኞችና ሰልጣኞች ናቸው፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ተገኝተው ካደረጉት የቁሳቁስ፣ የስንቅና የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ዛሬም የማስልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች እና የገነት ሆቴል በለሙያዎች ጥምረት ቦታው ድረስ ሄደው ለመከላከያ ሰራዊት አባላት በጊዜያዊ ማረፊያ ሥፍራ እና በደብረ ብርሃን ከተማ ሆስፒታል የሚገኙ በጦርነቱ ሰቢያ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን የምሳና የእራት ፕሮግራም በማዘጋጀት ምገባ አካሂዷል፡፡
በእራት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል እና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ ለመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ክብርት ሙፈሪያት ካሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የእናንተን ውለታ በገንዘብ፣ በቁስ መተካት አይቻልም ውድ ህይወታችሁን እየሰጣችሁ በጀግንነት ሀገር የምታቆዩ ናችሁ፤ ነገር ግን አለን፣ አይዟችሁ፣ በርቱ ብለን ደጀን ለመሆንና ምስጋና ለማቅረብ ነው እዚህ የተገኘነው ብለዋል፡፡ በዞኑ የመከላከያ ሰራዊት አስተባባሪ ሌ/ኮሎኔል አብዲ ሙሳ እና ኮሎኔል ዶ/ር ዓለሙም እየተደረገ ላላው ድጋፍ እና አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር አክለውም በሁሉም መስክ ድጋፋችን አሁንም ይቀጥላል፤ ሀገር ወደፊት ትቀጥላለች እጃችንን እየጠመዘዙ እንደፈለገን እናድርጋችሁ የሚሉንን የውጭ ሀይሎች ደግሞ ባለን የሰው ሃይል ተጠቅመን ድህነታችንን አሸንፈን በኢኮኖሚ ቀና እንድንል በርካታ የሥራ ዕድሎችን የምትፈጥር ሀገር እንድትኖረን አጥብቀን እንሰራለን ብለዋል፡፡
የምግብ ዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ ሰልጣኞች የተቋሙ ሰራተኞችና የገነት ሆቴል ባለሙያዎች በበኩላቸው ስለ ዝግጅቱ ሲጠየቁ የምንሰራው ለሀገሩ ክብር ለሚዋደቀው የመከላከያ ሰራዊታችን በመሆኑ ደስተኞች ነን፣ ሀገር የወታደር ብቻ አይደለችም፤ የሁሉም ናት፤ ሀገር ችግር ውስጥ ስትሆን ደግሞ አያገባኝም ማለት አንችልም፤ እስካሁን የተደረጉት ዝግጅቶች ላይም በደስታ እየተሳተፍን ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በመጨረሻም የብሔራዊ ቲያትር የባህል ሙዚቃ ቡድን አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን የመከላከያ ሰራዊቱን አዝናንተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ አስካሁን ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርገዋል፡፡