የሲዳማ ክልልን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችንና ባህላዊ ዕሴቶችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ጥቅል የጉዞ ፓኬጅና የቱር ማፕ (Tour package and Tour map) በማሰልጠኛ ማዕከሉ ተዘጋጀ፡፡

በአገራችን ለ34ኛ ጊዜ በሲዳማ ክልል የሚከበረውን የዓለም ቱሪዝም ቀንን ምክኒያት በማድረግ የክልሉን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የሆኑ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን፣ ባህላዊ ዕሴቶችን ማስተዋወቅና የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችል “Tour package and Tour map” በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ለማኔጅመንት አባላት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ይህ ጥቅል ፓኬጅ በውስጡ 12 ሰነዶችን የያዘ ሲሆን ሀዋሳን እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ አድርጎ የጎብኝዎችን ቆይታ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ማራዘም የሚችል እንደሆነ የቡድኑ አስተባባሪ አቶ አለምነህ መርሻ ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የሆኑ ባህሎችና ዕሴቶች ባለቤት ሲሆን ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀቱ ፣የዕርቅ አፈታት ዘዴውና ተፈጥሮን የሚጠብቁበት ዘዴ እራሱን የቻለ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ እንደሆነና እስከ ዛሬ ክልሉም ሆነ አገራችን በዚህ ዘርፍ ያልተጠቀመችበት መሆኑን የቡድኑ አባል አቶ በቀለ ኡማ ገልጸዋል፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የማሰልጠኛ ማዕከሉ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የሰራው በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነ የጉዞ ጥቅል (የጉዞ ፓኬጅ) ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ሥራ መሰራቱንና በዚህ ስራ የተሳተፉትን ባለሞያዎች የተቋሙ አመራርና የማኔጅመንት አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀን ከመስከረም 12 እስከ 16 2014 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በሀዋሳ ከተማ የሚከበር ሲሆን ሲፖዚየም፣ ባህላዊ የምግብ ፌስቲቫል እና የከተማው ብራንድ ኬክ ዝግጅት ላይ ተቋማችን በልዩ ሁኔታ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡