የማሰልጠኛ ማዕከሉ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2014 ዓመት ዕቅድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ።

የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2014 ዓመት ዕቅድ የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የዕቅድ አፈጻጸሙን ያቀረቡት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ተቋሙ ካሉት ተልዕኮዎች በማሰልጠን ፣ በምርምርና ማማከር የተሠሩ ሥራዎችላይ ትኩረት በማድረግ ሪፖርት አቅርበዋል።
አክለውም በጥናትና ምርምር ዘርፍ በተቋሙ የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝ በቱሪዝም ዘርፍ ያደረሰውን ተጽዕኖ አስመልክቶ የተዘጋጀው ጥናት ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህን ተከትሎ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመገኘት በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶች የማማከር አገልግሎት መሰጠቱ የበጀት ዓመቱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ያቀረቡት የዕቅድና በጀት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ነገዎ የስልጠና፣ ጥናትና ምርምር እና የማማከር አገልግሎቶችን ለመስጠት የታቀዱ ስራዎችን ለውይይት መነሻ በሚሆን መልኩ አቅርበዋል።