“ይመኙን ይሆናል አያገኙንም ይሞክሩን ይሆናል አያሸንፉንም ” ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ሼፎች፣ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ጋር በገነት ሆቴል ለመከላከያ ሠራዊት ደረቅ ስንቅ አዘጋጅተዋል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ በተደረገው የስንቅ ዝግጅት ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል ተማሪና ሰራተኞቹ በሞያቸው ለማገልገል እና ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን ለመሆን ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው ኢትዮጵያ ላትመለስ ወደፊት የምትገሰግስበት ጊዜ ቅርብ ነው፤ ይህንን እውን ማድረግ የምንችለው አንድ ሆነን ጠንክረን በመማር እና በመሥራት በተሰማራንበት መስክ አሸናፊ ሆነን የዳበረ እና ነፃ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ተማሪዎቹ ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
ለተማሪዎቹ ሰላማችንን እናረጋግጣለን ብልፅግናችንን እውን እናደርጋለን ያሉት ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ኢትዮጵያውያንን “ብዙዎች ይመኙን ይሆናል ግን አያገኙንም፤ ይሞክሩን ይሆናል አያሸንፉንም” ሲሉ አረጋገጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የተመቸች አገር እንድትሆን እናደርጋለን በማለትም ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት የስንቅ ዝግጅቱ ኢትዮጵያ ለውስጥም ሆነ ለውጭ ኃይሎች የማትደፈር የጀግኖች አገር መሆኗን ለማሳየት እና ለሠራዊቱ አባላት አለንላችሁ ለማለት የታሰበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገጽ የተወሰደ