ታህሳስ 23/2013 ዓ.ም ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ማ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሆቴልና ቱሪዝም ስራዎችን አብሮ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አደረጉ፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከልና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አብሮ ለመስራት የሚያሰችል ሰነድ በምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ማዘንጊያ ሽመልስ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ በሥራ ላይ ያለውን ክፍተት አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ኢንዲሲትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል ማቅረብና በዘርፉ ምርምር፣ ማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ለሃገራችን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጾ ማድረግ የሚሉ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ ማህበራዊ ሣይንስና ሂውማኒቲ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ገብሬ ታፈረ እንደተናገሩት የቀረበው ሰነድ በጣም ጠቃሚ እንደሆነና ተቋማቸው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰጠውን ስልጠና ለማዘመን ከአንጋፋው ሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ጋር መስራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ ቀደምት የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል በዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆኑን ገልፀው አሁን በቀረቡላቸው አማራጮች በመጠቀም፣ ጥናቶችን አብሮ በማጥናት በቱሪዝም ዘርፍ ዕውቀት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ በኢትዮጵያ ካሉት የቱሪዝምና የሆቴል ትምህርት ከሚሰጡ 17 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ በመሆኑ እንደ ፓይለት ፕሮጀክት የተመረጠ በመሆኑ አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶችን በማዘጋጀት በዘርፉ ውጤታማ ሥራዎች መስራት የሚያስችል ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የሁለቱም ተቋማት የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
Recent Comments