ለችግር ተጋላጭ የሆኑ 50 ሴቶችን ለመጀመሪያ ዙር በቤት አያያዝና በምግብ ዝግጅት ስልጠና መስጠት ተጀመረ፡፡
ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ ሚያዚያ 8/2011 ዓ.ም የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልኛ ኢንስቲትዩት ከቂርቆስ ክ/ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በወረዳ 11 ውስጥ የሚገኙ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ 50 ሴቶችን ለመጀመሪያ ዙር በቤት አያያዝና በምግብ ዝግጅት የተግባር ስልጠና በመስጠት ያለባቸውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ስልጠና መስጠት ጀመረ ፡፡ ዘርፉ በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልገውና ሰልጣኞች በየደረጃው የሚሰጠውን ስልጠና ወስደው ውጤታማ በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲለውጡ አደራ ያስተላለፉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ናቸው፡፡ በዚህ ስልጠና የተካፈሉ ሴቶች ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ስራ አስኪያጅም ቃል ገብተዋል፡፡ በተመሳሳይም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ይህን ስልጠና በተቋሙ ታሪክ የመጀመሪያ በመሆኑ እናንተም በዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንድትሆኑና ለራሳችሁ የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ በመሆነን ራሳችሁን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ የምታወጡበት ተደራጅታችሁ ፈጣን ምግቦች፤ ዳቦና ኬክ የመሳሰሉትን በማዘጋጀት የተሻለ የምትጠቀሙበት በመሆኑ በትኩረት ስልጠናውን እንድትከታተሉ አሳስባለሁ ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ለዚህ ስልጠና መሳካት ጥረት ያደረጉትን ሰራተኞችና መምህራን አመስግነዋል፡፡ በመክፈቻው ሥነስርዓት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትርና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ከሆቴል ባለሙያዎች ማህበር፣ የአዲስአበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበርና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡ ስልጠናው ለሁለት ሣምንት የሚቆይ ሲሆን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ትምህርት በመስጠት የሚጠቃለል ይሆናል፡፡