ቱ .ኢ .ማ ታህሳስ 20/2014 ዓ.ም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ተልዕኮች አንዱ የማማከር አገልግሎት ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሙያዊ ድጋፍ፣ የማማከር አገልግሎት እና የስራ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

የቡድኑ ተግባር በዘርፉ እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ማሻሻል እና በክልሎቹ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ማህበራት እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት ጋር የስራ ትስስር መፍጠር ነው፡፡
ይህንን ተግባር እንዲያከናውን የተቋቋመው ከመምህራን የተውጣጣ ስድስት ቡድን ወደ ዘጠኝ ከተሞች በመጓዝ ሀዋሳና ወላይታ፣ አርባምንጭ፣ ኮንሶ ፣ ጅንካና ቱርሚ ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ እና ጅማ ከተሞች በመጓዝ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፎች ለሚሰሩ ባለሙያዎች የሥራ ላይ ስልጠና እንደሰጡ የየቡድኑ ሪፖርት አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡
በክልሎቹ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች፣ የሆቴልና ቱሪዝም ቢሮዎችና ዘርፍ ማህበራት እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት ጋር የስራ ትስስር ፈጥረው እንደመጡም ተገልጿል፡፡
ቡድኑ ሪፖርቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የተገኙት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት እንደገለጹት በአጭር ጊዜ እንደዚህ አይነት ስራ መሠራቱ እና ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በተግባር መፈፀሙ የሚያስመሰግን ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ በመረጃ የተደገፈው የቡድን ሥራ በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትና ከተቋማት ጋር የተደረገው አብሮ የመስራት ፍላጎት ህጋዊ ወደ ሆነ የስምምነት ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።