ታህሳስ 14/2015 ዓ.ም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚሰሩ ባለሙያዎች፣ ባለቤቶች ስለ ትብብር ስልጠና፣ ስለ ማሰልጠኛ ስነ ዘዴና ስለ ምዘና አመዛዘን ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ሰልጣኞችም በስልጠናው ወቅት በቡድን እና በግል ሆነው በሞጁል ዝግጅት፣ስለ ምዘና ሰነድ አዘገጃጀት የመሳሰሉትን ሥልጠናዎች በተግባር ከተለማመዱ በኋላ ያዘጋጁትን ሞጁሎች አስገምግመው፣ የጽሑፍ ፈተናም ተፈትነው ብቁ የሆኑት የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ሥልጠና በተቋማቸው ለሚላኩ የትብብር ሰልጣኞች የሚጠቅም መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ከየድርጅቶቹ አንዳንድ ሰው በዚህ ስልጠና መሳተፉ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ብቻ መሰልጠኑ ሰልጣኞቹ በሚመጡበት ጊዜ ላይገናኙ ይችላሉ ስልጠናውን የወሰደው ሰው በቦታው ላይኖር ቢችል፤ ሁለት ወይም ሶስት ሰው ቢሆን ይህን ክፍተት መሙላት ይችላል ብለዋል፡፡ በቀጣይ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሚኖር ስልጠና ተወካዮች እንደሚልኩ ቃል ገብተዋል፡፡
አክለውም የትብብር ሰልጣኞች ከመላካቸው በፊት የጋራ የትግበራ ዕቅድ ማውጣት ይገባል ብለዋል፡፡ በወሰድነው ስልጠና እና ተሞክሮን በማቀናጀት ሰልጣኞችን በጋራ መከታተል እና ብቁ ባለሙያ ማውጣት አለብን፤ ብቁ ባለሙያ ማውጣት የአንድ ወገን ኃላፊነት ብቻ አይደለም ብለዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር እና ማማከር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ከሰልጣኞች ስለቀረበው አስተያየት አመስግነው ለተነሱ ሃሳቦችም ግብረ መልስ በመስጠት አሁን የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው ለተሳተፉ ባለሙያዎችም የምስክር ወረቀት በመስጠት ሥልጠናውን አጠናቀዋል፡፡
በስልጠናው 60 ያህል ተሳታፊዎች የጀመሩ ሲሆን 54 ያህሉ አጠናቀዋል፡፡

Recent Comments