አገራት በቱሪዝም ዘርፍ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡት ባላቸው የመስህብ ብዛት ብቻ አይደለም።
ከቱሪዝም የሚገኝ የሀብት መጠናቸው የሚያድገው፣ ለመጎብኘት ተመራጭ የሚሆኑት መዳረሻዎችን በማልማታቸው፣ በበቂ ሁኔታ በማስተዋወቃቸው ብቻም አይደለም።
ከፍተኛ የጎብኚዎች ፍሰት የሚያስተናግዱ የዓለማችን ቀዳሚው አገራት ተፈላጊነት በሚሰጡት መስተንግዶና ባላቸው ቅንጡ ሆቴሎች ብዛትና በእንግዳ ተቀባይነታቸውም አይደለም። እነዚህ አገራት የጎብኚዎችን ቀልብ ስበው፣ በየዓመቱ ሚሊዮኖች ወደ አገራቸው የሚተሙበት ዋንኛ ምክንያት ለቱሪስቶች በሚሰጡት የደህንነት ዋስትና እና በአገራቸው ባለው የሰላም አየር ምክንያት ነው።
በእርግጥ ቀልጣፋና ጥራት ያለው መስተንግዶ፣ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ በቱሪስቶች ተመራጭ የመስህብ ስፍራ፣ የታሪክ፣ የባሕል፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን አካባቢ ለመጎብኘትና ቆይታ ለማድረግ የሚያስችል መዳረሻ ልማት ለቱሪዝም እድገት በእጅጉ አስፈላጊና ወሳኝ ናቸው። ይሁን እንጂ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ቱሪስቶች ደህንነት ተሰምቷቸው ቆይታ አያደርጉም። በእነዚህ ምክንያቶች የዘርፉ ባለሙያዎች ሰላም ለቱሪዝም፤ ቱሪዝም ደግሞ ለሰላም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ።
አቶ ገዛኸኝ አባተ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በኢትዮጵያ ለ37ተኛ ጊዜ ‹‹ቱሪዝምና ሰላም ›› በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በማስመልከት ተቋማቸው ባዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ ሰላምና ለቱሪዝም ተመጋጋቢና አንዳቸው ለአንደኛቸው በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እና የመስህብ ስፍራዎችን ለመጎብኘት፣ አገልግሎት ሰጪዎችም የጎብኚዎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ የተሟላ መስተንግዶ ለማቅረብ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል። በዚህ ምክንያት ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያለው ቱሪዝም እንዲነቃቃ ለማድረግ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።
የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በከተማና በገጠር ያለውን የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይጠቁማሉ። ዘርፉ የስራ እድል ለመፍጠር ካለው ከፍተኛ አቅም ባሻገር ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ለመጠበቅ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ የሚያስችል ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ መሆኑንም ያመለክታሉ።
ያልተነካ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑም በእቅድ ከተሰራ አስተማማኝ የስራ እድልና ሀብት የሚፈጥር መሆኑ እንደሚታመንም ይናገራሉ። ዘርፉ ካለው የአካታችነት ባህሪ አንፃር በመንግስት፣ በግሉ ዘርፍና በሲቪክ ማህበረሰቡ መካከል ሊኖር የሚገባውን የትብብርና የስራ ጥምረት የማጎልበት አቅም እንደሚፈጥር አስገንዘበዋል።
ቱሪዝም ከዚህ የአካታችነት ባህሪው ባሻገር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በአንድነት በማሰባሰብ ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጠናከር፣ የባህልና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር እንደሚያደርግ የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ሰላም በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ። ሰላምና መረጋጋት ለቱሪዝም እድገት ወሳኝነት እንዳለው ተናግረው፤ በተቃራኒው ቱሪዝም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያካትት እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጆች የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉና በመካከላቸው መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በማስቻል ለሰላም መስፈንም የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል። ከዚህ አንፃር ሁሉም የመስኩ ባለድርሻዎች ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ሰላም ለቱሪዝም፤ ቱሪዝም ደግሞ ለሰላም የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ መረባረብ ያስፈልጋል ይላሉ።
አቶ ሳህለ ተክሌ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ምሁር ናቸው። በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል። የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ‹‹ሰላምና ቱሪዝም›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ባዘጋጀው ፓናል ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል። እርሳቸውም፤ ሰላምና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ አንዳቸው ለአንዳቸው በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆኑ ይገልፃሉ።
ለቱሪዝም እድገት ሰላም ያለው ከባቢ መኖሩ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውና አስፈላጊ ነው የሚሉት ጥናት አቅራቢው፤ ሰዎች ከቦታ ቦታ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የመስህብ ስፍራዎችን ለመጎብኘት እንዲሁም መስህቦቹ የሚገኙባቸው ቦታዎችም እንግዶችን ተቀብለው ለማስተናገድ ሰላም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ የቱሪዝም እድገት መኖሩ በራሱ ሰላም እንደሚያመጣ፣ ሰዎች የስራ እድል ሲፈጠርላቸው፣ ማህበረሰቡ የኢኮኖሚ አቅሙን ባሉት የመስህብ ሀብቶች ሲያሳድግ በተመሳሳይ ለሰላም መኖር አስተዋፆኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ።
‹‹ቱሪስቶች በቀላሉ ሰላም እንዳለ ሊገምቱ የሚችሉባቸው አገራትን ተመራጭ ያደርጋሉ›› የሚሉት ጥናት አቅራቢው አቶ ሳህለ ተክሌ፤ ማንኛውም ቱሪስት በደህንነቱ እንዲሁም ምን ሊፈጠርበት እንደሚችል እርግጠኛ ወዳልሆነበት አካባቢ ለጉብኝት መሄድ ምርጫው እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ቱሪዝም ከሌሎች ዘርፎች በተለየ በትንሽ አለመረጋጋትና ሰላም እጦት ተፅእኖ ስር የሚወድቅ ፍፁም ሰላምን የሚፈልግ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የውስጥ አለመረጋጋት፣ ደህንነትን አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ስፍራዎች፣ ዘረፋ እና ሌሎች መሰል በቀጥታ ከሰላም እጦት ጋር የሚገናኙ ጉዳዮች የሚፈጠሩ ከሆነ የቱሪስቱ ፍሰትም እንደሚያሽቆለቁል አጠቃላይ የቱሪዝሙ እድገት እንደሚቀንስ ያስረዳሉ።
የሰላም እጦት በቱሪዝም መሰረተ ልማት እና በቱሪስት ፍሰት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ለመረዳት ሶሪያን፣ ግብፅን፣ ማሊን እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ጥናት አቅራቢው፤ ሶሪያ ዘመናትን የተሻገሩ ቅርሶች በአይ ኤስ አይ ኤስ ሽብርተኛ ቡድን መውደሙና የቱሪስት ፍሰቱ በ94 በመቶ መቀነሱ እንዲሁም ኢኮኖሚ ተፅእኖው በእጅጉ ለማሽቆልቆሉ ምክንያት መሆኑን አብነት ጠቅሰው አብራርተዋል። በግብፅም በአረብ አብዮት በ2011 የቱሪስት ፍሰቱ በ95 በመቶ ቀንሶ እንደነበር አስታውሰው፣ በሲሪላንካና በማሊም በውስጥ አለመረጋጋት እና የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳደረሰ በአስረጂነት ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያ የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተ ወቅት ቱሪዝሙ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሮበታል የሚሉት ጥናት አቅራቢው፤ ከዚያ በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ፖለቲካን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች መፈጠራቸው ለቱሪስት ፍሰት መቀነስ ምክንያት ስለመሆናቸውም አመልክተዋል።
መንግሥት ቱሪዝምን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ማድረጉና ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ አንድ በጎ ጅምር መሆኑንም ጠቅሰው፣ በአገሪቱ የሚታየው አለመረጋጋት በቀጥታ በእድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑን ያመለክታሉ። መንግሥት በቱሪዝም ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ በተቃራኒው ግጭቶች ደግሞ ለጎብኚዎችና ለዘርፉ እድገት ጋሬጣ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በየአካባቢው የሚፈጠሩ ፖለቲካን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የተጀመሩ መነሳሳቶች ውጤት ሲያሳዩ፣ ይህም መንግሥት ለዘርፉ እየሰጠ ካለው ከፍተኛ ትኩረት ጋር ሲደመር በቅርብ ጊዜ ውስጥ በጎ ውጤት ይመዘገባል ሲሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ጥናት አቅራቢው ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የታሪክ እና የሌሎች የዓለም ቅርስና መስህቦች ባለቤት እንደሆነች ይናገራሉ። ይህንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም አገራዊ እርቅ በማድረግ፣ የተረጋጋ ከባቢን በመፍጠር የጎብኚዎችን ቀልብና እምነት ሙሉ በሙሉ በማግኘት ቱሪዝም ለኢኮኖሚና ለማህበረሰብ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፆኦ ማሳደግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
አቶ ዳንኤል ወርቁ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣንን በመወከል በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፤ እርሳቸው የጥናት አቅራቢውን ፅሁፍ እና የውይይቱን ርእሰ ጉዳይ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት እሳቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላም እጦት ምክንያት በዓለማችን ላይ በበርካታ አገራት የቱሪዝም እድገትና የቱሪስት ፍሰት እያሽቆለቆለ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችም ይገልፃሉ።
አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ተወዳዳሪ የሚሆነው ከመለኪያዎቹ ውስጥ አንዱ የሆነውን የሰላምና የደህንነት መስፈርትን ሲያሟላ እንደሆነ አቶ ዳንኤል አስታውቀው፣ ሰላምን ማረጋገጥ እና ለቱሪዝሙ እድገት መሰረት መጣል ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ።
ጎብኚዎች ከቤታቸው የሚወጡት ተጨማሪ ሰላምን ፍለጋ እንጂ ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ስጋት ውስጥ ለመክተት አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ለጎብኚዎች ምቹ ከባቢ መፍጠር ቀዳሚ መሆኑን አስገንዝበዋል። አገራት በሰላም እጦት ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚደርስባቸው እንደ ምሳሌ በማንሳትም ሲሪላንካ እ.ኤ.አ በ2019 ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማጣቷን ይጠቅሳሉ።
‹‹ሰላም ከሌለ መስህቦች ላይም ጉዳት ይደርሳል›› የሚሉት የዱር እንስሳት ጥበቃ ተወካዩ አቶ ዳንኤል፤ ይህን ተከትሎም የስራ አጥ ቁጥር እንደሚጨምር፣ የቱሪዝም እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያርፍና ድህነት እንደሚባባስ ይህም ወደ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንደሚወስድ አብራርተዋል። በእነዚህ ምክንያቶች ሰላም ለቱሪዝም ቱሪዝም ደግሞ ለሰላም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ለእነዚህ ጉዳዮች ሁሉም ባለድርሻዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች ጥናታዊ ፅሁፉን መነሻ በማድረግ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከሚያበረክ ተው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፆኦ ጋር በተያያዘ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ እንደሚባል አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቅሰው፣ ይሁን እንጂ በሰላም ምክንያት በሚፈጠር ስጋት ጎብኚዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚታዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን እንደ ሽምግልና ባሉት ባህላዊ ስርዓቶች በእርቅና በመሳሰሉት በመፍታት ሰላምን መመለስና የቱሪዝሙን እድገት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተነስቷል።
ሁሉም ዜጎች የአገራቸውን ገፅታ ሊገነባ በሚችል መልኩ የሰላም ዘብ መሆን እንደሚገባቸውም በተሳታፊዎቹ ተጠቁሟል፡፡ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ አንስቶ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው የተመላከተ ሲሆን፣ በተለይ የአገር ገፅታን ሊያጠለሹ በሚችሉ ድርጊቶች ላይ ባለመሳተፍ ለዘርፉ አስተዋፆኦ ማበርከት እንደሚገባ ተገልጧል። አንድ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ በሚገባበት ወቅት ከአየር መንገድ አንስቶ እስከሚያርፍበት ሆቴል ድረስ እንዲሁም በሆቴልና የጉብኝነት ቆይታው እስኪጠናቀቅ ደህንነቱን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጪዎቹ አስገንዝበዋል።
በዳግም ከበደ https://press.et/?p=138488
መረጃው ከEthiopian Press Agency /የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም
Recent Comments