ሚያዚያ 12/2015 ዓ.ም ቱ.ማ.ኢ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለ21 ቀናት ሲሰጥ የቆየውን ወደ ሳውዲ አረቢያ ለቤት ውስጥ ሥራ የሚሄዱ ሰልጣኞችን ሲኦሲ በማስመዘንና የምስክር ወረቀት በመስጠት አጠናቀቀ፡፡

ስልጠናው በምግብ ዝግጅት፣በላውንደሪና ቤት አያያዝ፣ መሰረታዊ የእንግሊዝኛ እና የአረቢኛ ቋንቋ፣
ኢንተርፕሪነሺፕና ገንዘብ አያያዝ እንዲሁም ሥነ ምግባርና ወደውጪ ከመሄዳቸው በፊትና ከሄዱ በኋላ ስለሚኖር የስነልቦና ዝግጅት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ከዚህ ቀደም በመካከለኛው ምስራቅ ለሥራ ሄደው የተመለሱ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳውዲ ለመሄድ ስልጠናውን ከተካፈሉ ሲሆኑ፤ ለተመላሾቹ የ90 ሰዓት ስልጠና ተሰጥቶ የሲኦሲ ምዘና ወስደው ስልጠናውን የተከታተሉት 29 ሴቶች አልፈዋል፡፡
ይህንኑ ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳውዲ ለመሄድ ስልጠናውን ከተካፈሉ 50 ሴቶች የ168 ሰዓት ስልጠና ወስደው በሲኦሲ ምዘና 41 ሴቶች አልፈዋል፡፡
ይህ ስልጠና በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለ ሲሆን ዜጎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሙያን መሰረት ያደረገ ሥልጠና ሲሰጥ በመሆኑ፤ ዜጎቻችን ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት የሙያ ክህሎት እንዲኖራቸው በመላው አገሪቱ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በከፍተኛ ትኩረት ሥልጠናው እየተሰጠ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
መንግስት ዜጎቹ ወደ ውጭ ለሥራ መሄድ ከፈለጉ በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ እና ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ብሎም የአገራቸውን ስም እንዲያስጠብቁ ለማድረግ በስልጠና ውስጥ አልፈው ብቃታቸውን አስመስክረው መሄድ እንዲችሉ የስልጠና ተቋማት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ሞጁል በማዘጋጀት እና በማሰልጠን እንዲሁም በማስተባባር ሰልጠናው እንዲሳካ ያደረጉትን አሰልጣኞች ክቡር አቶ ጌታቸው አመስግነዋል፡፡
ስልጠናውን ያጠናቀቁ እና በምዘና ያለፉት ሴቶች የከተማ አስተዳደሩ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ እና ክፍለ ከተሞች ከጉዞ ጋር ያሉ ተያያዥ ሥራዎችን እንደሚያጠናቅቁ የቂርቆስ ክ/ከተማ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፌቨን ተናግረዋል፡፡