ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ ጥቅምት 01/2012
ላለፉት 50 ዓመታት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን በማፍራት አንጋፋ ተቋም የሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ2012 ዓ.ም ዕቅዱን ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ ውይይት እያካሄደ ነው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት የኢንስቲትዩቱን ተማሪዎች ቀጣሪ በሆኑ ተቋማት ላይ ጥናት በማስደረግ ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ኢንስቲትዩቱ በሚመደብለት በጀት የሚሰራውንም ስራ የባለድርሻ አካላት ፍላጎት የተካተተበት እንዲሆን መድረኩ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።

የኢንስቲትዩቱን የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አቶ ተመስገን በቀለ ካቀረቡ በኋላ ውይይት ተካሂዶበታል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሀገራችን እየታየ ያለው ስራ ለዘርፉ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የአንድነት ፓርክ መከፈትና የሸገር የወንዝ ዳርቻ ልማት መጀመር ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ቱሪዝም ላይ እየሰሩ ያሉትን ሥራ በሚመጥን ደረጃ በዘርፉ የተሰማራን አካላት አብረን መራመድ ይገባናል ብለዋል ።

ኢንስቲትዩት የማይተካውን የሰው ኃይል በዘርፉ የሚያመርት በመሆኑ ብቃት ያለው ባለሙያ ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተጠቁሟል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት በማሸነፋቸው የተስማቸውን ደስታ በውይይቱ መክፈቻ ላይ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ገልፀዋል ።