ነሐሴ 29/2015 ዓ ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜ አንድ ”የአገልግሎት ቀን ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል ፤ ቀኑን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን በተዘጋጀ ዙሪያ ሰነድ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህ ፕሮግራም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋማችን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት የዛሬው ስብሰባ ዋና ዓላማ ጳጉሜ 1 ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት ቀን በሚል መሪ ቃል የተቋሙ ሠራተኞች እና አመራሮች ለተገልጋዮቻችን አገልግሎት በመስጠት እንዲከበር በመታቀዱና ለዚሁ እንዲያግዝ ቀደም ብሎ ሁሉም የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች የሚሳተፉበት የፓናል ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል ።
አቶ ጌታቸው አክለውም ሁሉንም የመንግስት ሠራተኛ በሚያሳትፍ መልኩ ጳጉሜ በተለያዩ አጀንዳዎች እንዲከበር ሲወስን በየመስሪያ ቤቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተገናኙ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ ሀሳቦችን በማፍለቅ በቀጣይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የተቋሙ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋገኘሁ ለገሠ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመልካም አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦችን የያዘ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ ከሰራተኞች ጥያቄና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በተለይ ተቋማችን አገልግሎት ሰጪ በመሆኑ ከተገልጋይ የሚመጡ ቅሬታዎችን መፍታት እንደሚጠበቅብን ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም በመንግስት ሥራ ለ40 እና ከዚያ በላይ ዓመት አገልግሎት ለሰጡ የተቋሙ ሶስት ሰራተኞች ስለ መልካም አገልግሎታቸው የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ረቡዕ ጳጉሜ 1/2015ዓ.ም ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤት አመራር እና ሠራተኞች ከጧቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ በሥራ ገበታቸው ላይ በመገኘት በምንም ዓይነት የስብሰባ አጀንዳዎች ሳይጠመዱ ቀኑን በአገልጋይነት የሚያሳልፉበት ዕለት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡