ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ ነሐሴ 28/2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን መደ ወላቡ ወረዳ አዲስ የዋሻ ቅርስ መገኘቱ ተገለፀ። ዋሻው በመደ ወላቡ ወረዳ ሊቂምሳ ቦኮሬ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዋጫራ ሀይቅ በመባል በሚጠራ አካባቢ መገኘቱ ነው የተነገረው።
አዲስ የተገኘው ዋሻ “መነ ዋቃ (የእግዜር ቤት)” በመባል እንደሚታወቅም ዋሻውን በጥናት ያገኘው የመደ ወላቡ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከመደ ወላቡ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ አዲስ የተገኘው ዋሻ 47 የመግቢያ በሮች አሉት።
ዋሻው በድሮ ዘመን ሙዴ ገልቹ በተባሉ ሰው የአምልኮ ስርዓት ይፈፀምበት እንደበረም ከአካባቢው አዛውንቶች መረጃ ማግኘቱንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
ዋሻው “መነ ዋቃ (የእግዜር ቤት)” የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከዚሁ ተነስቶ እንደሆነም ነው የአካባቢው አዛውንቶች የሚናገሩት።
የመደ ወላቡ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቅርስ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ሀይደራ ኢብራሂም የተመራ ቡድን ዋሻው ካሉት 47 መግቢያ በሮች በአንዱ በመግባት በውስጡ ምልከታ አደርጓል።
በዚህም በዋሻው ውስጥ ሰፊ አዳራሽን ጨምሮ የኦዳ፣ የዋንጫ፣ የሴት ልጅ ጡት እና የላም ጡት ቅርፃ ቅርጾችን የተመለከቱ ሲሆን፥ ቅርጻ ቅርጾቹ በአረንጓዴ፣ በነጭ እና በቀይ ቀለማት የተዋቡ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የዋሻውን ርዝመት ለመመልከት ለ3 ሰዓታት ያክል በዋሻው ውስጥ የግር ጉዞ የተደረገ ሲሆን፥ ዋሻው ውስጥ ካለው ድቅድቅ ጨለማ የተነሳ መጨረሻው ላይ መድረስ እንዳልተሻለም ተገልጿል።
የዋሻው የውስጠኛ ክፍል በርካታ መንገዶች ያሉት እንደሆነም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
የመደ ወላቡ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቅርስ ባለሙያው፥ አሁን የተካሄደው ጥናት የግኝት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ ግን የተለያዩ ጥናቶች በስፋት እንደሚካሄድበት አስታውቀዋል።
ምንጭ ኤፍ.ቢ.ሲ
Recent Comments