ቱ. ማ. ኢ የካቲት 22/2015 ዓ.ም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በአራት የተለያዩ መስኮች የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊዘጋጁ ነው፡፡

እነዚህ ጥናትና ምርምር ሥራዎች በተቋሙ መምህራን የሚከናወኑ ሲሆን፣ ጥናቱን ለማስጀመር ለተዋቀሩት የጥናት ቡድኑ አባላት የሥራ መመሪያ የሰጡት የተቋሙ የጥናት ምርምርና ማማከር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እንደገለጹት እነዚህ ጥናቶች ወደ ተግባር የሚቀየሩ፣ ውጤታቸውም ተቋም ዘለልና ሀገር አቀፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው ጥናት ባለፉት ዓመታት በተቋሙ የነበረውን ስልጠና የሚዳስስ፣ ሰልጥነው የተመረቁ ባለሙያዎች፣ የስልጠና ጥራት ለማሻሻልና ብቁ እና ሥራ ፈጣሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት መሰረት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ ይህ ጥናት በተቋሙ እየተተገበረ ለላው የዓለም ባንክ ፕሮጀክት አንዱ ቅድመ ሁኔታ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ሁለተኛው ጥናት ደግሞ በቱሪዝም ዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ይህም ለቱሪዝም ሚኒስቴርና ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለፖሊሲ ግብዓት ጭምር የሚሆን ሲሆን፣ ሶስተኛው የጥናት ክፍል በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያለውን የስልጠና ጥራት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በማጥናት ለማሸጋገር ያለመ ነው፡፡
በአራተኛ ደረጃ የተያዘው ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የሚያተኩረውና ከዚህ በፊት በሲዳማ ክልል ባህላዊ ምግቦችን በማጥናት ለስልጠና እና ለማስተዋዋቅ የተጀመረውን ሥራ በማስፋት የሌሎች ክልሎች መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ምግቦችን በጥናት በመለየት፣የምግብ አዘገጃጀት ስታንደርድ በማውጣት ወደ ባለኮከብ ሆቴሎች በሜኑ መልክ እንዲገቡ የሚያግዙ ስራዎች ናቸው፡፡
በዚህ መሰረት ለጥናት ቡድኑ አባላት የአንድ ቀን ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ ተቋሙን የልህቀት ማዕከል የሚያደርጉ እና ዘርፉን የሚያዘምኑ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር በመለየት ወደተግባር የመቀየሩ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ የጥናትና ምርምር ሥራ መሆኑ ይታወቃል፡፡