የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበጀት ስሚ መርሀ ግብር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የሚኒስቴሩ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የ2015 አመት የበጀት እቅዳቸውን አቅርበው በገንዘብ ሚኒስቴር ተገምግሟል፡፡
በግምገማው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሰመዘገብ በሚደረገው ጥረት የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎትን ለማሳደ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት በህጋዊ መንገድ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን በሚሄዱበት ሀገር ችግር እንዳይገጥማቸውና መሰረታዊ የቋንቋ፣ የምግብ ዝግጅትና የቤት አያያዝ እውቀት ኖሯቸው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማድረግ የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም የማሰልጠኛ ተቋም የሚያስፈለጉትን ግብአቶችን ለይቶና አዘጋጅቶ ቢያቀርብ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የሆኑት የቴክኒክና ሙያ ስልጠናና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ በላይ የ2015 የበጀት እቅድ ያቀረቡ ሲሆን በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ውስጥ በጀታቸውን አስተካክለው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ የገቢዎች ሚንስቴርና የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ባለስልጣን በመደበኛና ካፒታል የበጀት መደቦች የጠየቁት በጀት ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ በመሆኑ አስተካክለው እንዲያቀርቡና በመጪው በጀት ዓመት በገቢዎች ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ለማሻሻልና የቢሮ ህንፃ ግንባታ የቅድመ ዝግጅት ስራን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ያለበትን የተሸከርካሪ ችግር ለመቅርፍም ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥቅል ግዢ ሲፈፀም አብሮ ምላሽ እንደሚያገኝ አቶ አህመድ ሽዴ ጨምረው አመልክተዋል፡፡
Recent Comments