የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን የቱሪዝም አቅም ማሳየት የሚችል ጥናት፣ የጉዞ ካርታ እና የጉዞ ጥቅል መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኝ እምቅ የቱሪዝም ሀብትን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ጥናቶችን ከክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል፡፡
በአካባቢው ላይ የሚገኙ እምቅ አቅሞች የሚያሳይ ጥናት፣ ይህን በመከተል የጉዞ ካርታና ቱር ፓኬጅ መዘጋጀቱን የጠቀሱት ጥናቱ ከተሳተፉት መካከል የኢንስቲትዩቱ ምርምር ባለሙያ አቶ አህደር ጠና ክልሉ ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት ያለው ቢሆንም እንደ ሀገር በቂ ጥናት ተሰርቶ በሚገባው ልክ ለዓለም አላሳየንም ይላሉ፡፡
አካባቢው የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶችን የተጎናጸፈ ነው ብለዋል። በማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ አሁን የተጀመሩ ሥራዎች እንደ ሀገርም ሆነ ለክልሉ የቱሪስት ፍሰትን ይጨምራል፣ ማህበረሰቡም ከቱሪዝም ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል ይፈጥራል።
ከተጠቀሱት ጥናት ሥራዎች በተጨማሪ የምግብ ቱሪዝምን ሊያጠናክር የሚችል በክልሉ የሚገኙ ዞኖች ባህላዊ ምግቦች ሰነድ ዝግጅት መደረጉንም አቶ አህደር ገልጸዋል፡፡ በተለይ ይህ የምግብ ዝግጅት ሰነዶች መዘጋጀታቸው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎቻችን ውስጥ ኢትዮጵያዊጣእም ያላቸውን ምግቦች ቱሪስቱ እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል የሚሉት አቶ አህደር ጠና የሀገራችንን ምግብ ቱሪዝም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
ከተሰሩት ሰነዶች መካከል የስድስት ዞኖች ቱሪስት ማፕ፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እና አጠቃላይ የክልሉ ቱሪስት ማፕ መሰራቱን የገለጹት ባለሙያው የክልሉን ገጽታ የሚቀይር ትልቅ መሰረት የሚጥል ስራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ማሰልጣኛ ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር እያከናወናቸው የነበሩ ስራዎችና የአካከባቢውን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከህዳር 05/2017 ዓ.ም ጀምሮ በቦንጋ ከተማ የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/