የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ጥራት ማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን የሥራ እድል ለማስፋት የባለድርሻ አካላት የስራ ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን ስልጠና ጥራትን ለማሳደግ የተሰራ አዲስ የዲግሪ መርሀ ግብር ስርዓተ ትምህርትን ለመገምገምና በቀጣይ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር አገልግሎቶች ዘርፍ የሚሰሩ ተግባራት ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የመድረኩ ዋና አላማ ቀደም ስል የነበረውን በቅንጅት የተሰሩ ስራዎችን በመገምገምና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ምክክር ለማድረግ መሆኑን የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ የሆቴልና ቱሪዝም እንዱስትሪው እንዲዘምን ፣አገልግሎቱም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ፣ዘርፉም ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጥር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና የስራ ትብብር ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በተለይም የክህሎት ስልጠናዎችን ለመስጠት ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ሙሉ ተሳትፎ ውጭ የሚታሰብ አይደለም ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማቅረብ፣ በጥናትና ምርምር እና በማማከር አገልግሎት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ጌታቸው ነጋሽ ከዘርፉ አገልግሎት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በገበያው ላይ የሚታየውን ሰፊ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ላይ በቅንጅት የተሰሩ ሥራዎችና የቀጣይ ጊዜ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዝርዝር የቀረቡ ሲሆን የተቋሙ ስልጠናና አቅም ግንባታ ም/ዋ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት እና የምርምርና ማማከር ዘርፍ ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም በየዘርፋቸው በተቋምና ከተቋም ውጭ የተከናወኑ ተግባራት አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ በጋራ ከሰራባቸው ተቋማት መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ኮንታ ዞን ጭዳ ኮሌጅ ተሞክሯቸውን አቀርበዋል።
በዚህ ምክክር መድረክ የተቋሙ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱን ጨምሮ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የኢንስቲትዩቱ ቦርድ አባላት፣የሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ዘርፎች ማህበራት እና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳትፈውበታል።
ውድ የገጻችን ተከታዮች ላይክና ሼር በማድረግ መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን ።