የምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ትራንስፎርሜሽን ቀጠናዊ ትስስር ፕሮጀክት(EASTRIP) የእቅድ ክለሳ ውይይት ተካሄደ፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ትራንስፎርሜሽን ቀጠናዊ ትስስር ፕሮጀክት(EASTRIP) በ2024 እ.ኤ.አ ይጠናቀቅ የነበረው ፕሮጀክት እስከ ታህሳስ 2026 ድረስ እንዲቆይ የእቅድ ክለሳ ውይይት ተካሄደ፡፡
በሀገራችን ስምንት በሚሆኑ ተቋማት ላይ እየተተገበረ የሚገኘው ፕሮጀክቱ የተያዙ ዕቅዶችን ለማጠናቀቅ እንዲያስችል በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ የሚሰሩ እቅዶች እና ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ ሥራዎች ላይ የዓለም ባንክ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በፕሮጀክቱ ደጋፊነት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሀገራዊ ጉዳዮችን እየሰራበት የሚገኝ ሲሆን በተለይ በስድስት ወራት ውስጥ የተከናወኑ ሥራዎች በመድረኩ ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ዕቅድና ሪፖርቱን ያቀረቡት በኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አብርሃም ለገሰ ተቋሙ በቀጣይ ለመስራት ካቀዳቸው ሥራዎች መካከል የግንባታ ሥራን ለማከናወን ትልቅ እድል እንዳለው አብራርቷል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሀገር ደረጃ ቱሪዝም ላይ ብቻ በማተኮር ስልጠና እየሰጠ የሚገኝና በዘርፉ ጥናትና ምርምር እየሰራ የሚገኝ ብቸኛ የመንግስት ተቋም በመሆኑ የሀገራችንን ቱሪዝም ለማሳደግ ለተቋሙ ዕቅዶች መሳካት በፕሮጀክቱ የሚደረግ ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የታቀደውን የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ በቁርኝነት እንደሚሰሩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከዓለም ባንክ ከመጡት የሥራ ኃላፊዎች መካከል ዶክተር ሽየን ሊያን (Dr. Xiaoyan Liang) በመድረኩ ላይ የቀረቡ የእቅድ አፈጻጸምና ዕቅዶችን ለማሳካት ሁሉም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው የነበረው አፈጻጸም ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የድሬደዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እና ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ትክክለኛ የኢንስቲትቱን መረጃዎችን ለማግኘት
የኢንስቲትዩቱን ፌስቡክ ገጽ https://www.facebook.com/tticommunication ወይም
ቴልግራም https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት https://www.tti.edu.et/ ይጎብኙ
Recent Comments