የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለ9ኛ ጊዜ ቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ቀጥሏል፡፡ በዛሬው ዕለትም በገነት ሆቴል ሶስት ርዕሰ ጉዳይ ያላቸው ከመሪ ቃሉ ጋር የተገናኙ ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡

ስፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ ቱሪዝም ለአብሮነት በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን አስታውሰው ቱሪዝም በባህሪው ድንበርና ወሰን የሌለው በመሆኑ ዘርፉን ከፍ የሚያደርገው አብሮነት በመሆኑ አሁን ዓለማችንም፤ አገራችንም ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ይህን አብሮነትን፣ አንድነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነገር ላይ ማተኮር ወቅቱ ያስገድዳል ብለዋል፡፡
የዚህ ሲፖዚየም አቅራቢዎች “ቱሪዝም ለአብሮነት” በቱሪዝም ሚንስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ፣ “ሙሉ የማህበረሰብ ኢኮ ሎጅ” የኢኮ ሎጁ መስራች አቶ ዓብይ ዓለም እንዲሁም “የሚዲያ ሚና ለቱሪዝም” በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አስናቀ ብርሃኑ ናቸው፡፡
አቶ ይስፋልኝ ባቀረቡት ጽሑፍ ቱሪዝም ከሰላም ጋር ፣ቱሪዝም ከአብሮነት ጋር ያለውን የተሳሰረ ግንኙነት ያነሱ ሲሆን አብሮነትን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ አስዋጽኦ እዳለው ጠቁመዋል፡፡
የሙሉ ኢኮሎጅ ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጮቄ ተራራን ተከትሎ የተሰራ የማህበረሰብ ሎጅ መሆኑንና አሁን ሎጁ ያለበትን ሁኔታ የነሱን ተሞክሮ ወደሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ማዳረስ የሚቻልበትን ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡
ከባህልና ቱሪዝም ሚዲያ ፎረም ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሃኑ በበኩላቸው የሚዲያ ሚና ከቱሪዝም አንፃር ያለውን ፋይዳ አንስተው ነገር ግን እኛ ያለንን የቱሪዝም ሃብት በበቂ ከማስተዋወቅ እና ዘርፉ በገጽታ ግንባታ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና ከማሳየት ላይ ውስንነት አለ ብለዋል፡፡
ሲፖዚየሙ በበተለያዩ የመድረኩ ተሳታፊዎች አስተያየትና ለሚመለከታቸው አካላት መልዕክት የተላለፈበት ነው፡፡
ዘጠነኛው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ነገ በተለያዩ የክህሎት ውድድሮች ቀጥሎ ይውላል፡፡