“ቱሪዝም ለሀገራዊ መግባባት “11ኛው የክህሎት ውድድርና መስተንግዶ ሳምንት መሪ ቃል ሰኔ 4/2016 ዓ ም

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 11ኛውን የክህሎት ውድድርና መስተንግዶ ሳምንት ቱሪዝም ለሀገራዊ መግባባት ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከናወነ ይገኛል።
በፕሮግራም መክፈቻው የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ዴኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ እንደገለጹት ለቱሪዝም ከተሰጠው ትኩረት አንጻር በክህሎት የተደገፈ ስልጠና ማድረግ ውጤቱን የጎላ ያደርገዋል ብለዋል። በሀገራችን በተለያዩ አከባቢዎች የቱሪስት መዳረሻዎች እየተሰሩ በመሆኑ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ይህንን ያልተቋረጠ የክህሎት ውድድርና የመስተንግዶ ሳምንት ለ11ኛ ዙር ማክበሩን አመስግነዋል።
የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚመጥን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት የተጀመሩ ሥራዎች መቀጠል እንዳለባቸው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው “ቱሪዝም ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጀቶች እንደሚከበር ገልጸው የአፋር፣ የሀረሪ፣ የሲዳማ እና የጋምቤላ እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ብሔር ባህላዊ ምግቦቻቸውን ወደ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ለማሸጋገር የሚያስችል የምግብ ፌስቲቫል መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ሌላው በቱሪዝምና በሆቴል ዘርፍ የሰልጣኞችና የአሰልጣኞች የክህሎት ውድድር መኖሩ በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ብሎም የሀገሪቱን ባህል ለማስተዋወቅ የሚያግዝ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም እንደ ሀገር በዘርፉ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲወዳደር ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅብን አመላካች ነው ብለዋል።
ለዚህ ይረዳው ዘንድ ተቋሙ በዘርፉ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ውጤቶችን ለማውጣት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ሁነቱ በሚካሄድባቸው ቀናት በባለሙያዎች መካከል ልዩ ልዩ የክህሎት ውድድር፣ ኤግዚቢሽንና፣ የበጎ አድራጎት እና ሲምፖዚየም ሥራዎች ይካሄዳሉ፡፡
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/