ታህሳስ 16/2015 ዓ.ም ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት እና ለመደገፍ የሚያስችል ጥናት በተቋሙ ባለሙያዎች አስጠንቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው፡፡

የውይይት መድረኩን የከፈቱት በሥራና ክህሎት ሚኒስትር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ እንደገለጹት መንግስት ልማትን ለማፋጠን በብዝሃ ዘርፍ መርህ የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ የኢኮኖሚ ፒላር አድርጎ በልዩ ሁኔታ እየሰራቸው ያሉ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች በሰለጠነ የሰው ሃይል ልማት መደገፍ አለባቸው፤ ለዚህ ደግሞ ተግዳሮቶቻችንና መልካም አጋጣሚዎችን በመለየት ወደፊት መራመድ የዚህ መድረክ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው በውይይቱ በመክፈቻ እንደገለጹት በዘርፉ የሚታየው የሰው ሀይል አቅርትና ፍላጎት ያለመጣጣም ችግር፣ በዘላቂነት ለመቅረፍ ሲባል ኢንስቲትዩቱ በሀገራችን የዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል በስፋት አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ስለሆነም በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፋችሁ ባለድርሻ አካላት ዘርፉን በማዘመን ለኢንደስትሪው የሚመጥን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር የሰው ኃይል ልማቱ ላይ በትኩረት መስራት እንድንችል በቅንጅት መስራት የሚያስችለንን ሥርዓት መዘርጋት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በሀገሪቱ የሚገኙ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዙሪያ ትምህርትና ሥልጠና የሚሰጡ ዩንቨርሲቲዎች ፣ የፖሊቴክኒክ ኮሌጆች፣ የክልል የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች እና ማህበራት ተሳትፈዋል፡፡ የጥናት ወረቀቶቹ ከሰዓት በኋላ በሚኖር መድረክ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡