በኮንታ ዞን የሚገኘውን የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ በሙያ የተደገፈ እንዲሆን ለማስቻል ሶስት መቶ ለሚሆኑ ወጣቶች በሆቴል ዘርፍ የአጭር ጊዜ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከኮንታ ዞን ጋር በመተባበር በዞኑ የሚገኘውን የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ በሙያ የተደገፈ እንዲሆን ለማስቻል በዓለም ባንክ ፕሮጀክት (EASTRIP) ድጋፍ በጭዳ እና አመያ ከተሞች በተግባር የተደገፈ የአጭር ጊዜ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በዞኑ በመንግስት እና በግል ባለሀብት እየለሙ ያሉትን የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ሀይል ለሟሟላት ከዞኑ ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ስልጠናና አቅም ግምባታ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት ስልጠናው በአካባቢው በሚገኘው ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡
በየአካባቢው የሚሰጡ እንደዚህ አይነት ክህሎት ተኮር ስልጠናዎች ለሀገር ኢኮኖሚ ክፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በመሆናቸው በሁሉም መዳረሻዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ አቶ ሀብታሙ ክብረት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አካባቢያችን ከገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አንዱ የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች የሚገኙበት ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ ያለበት ነው ያሉት የኮንታ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ደምሴ በዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል ስለሌለ በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ከማሰልጠን ባለፈም የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት በትብብር ስልጠና ብቁ እንዲሆኑ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር በ2015 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር በተሰጠው የአጭር ጊዜ ሥልጠና ብዙሃኑ ስራ መጀመራቸውን ያስታወሱት አቶ አበበ ደምሴ ከአካባቢው ብዙ ሰው የስራ እድል የሚያገኝ ከሆነ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የኔ ነው የሚል ስሜት ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የኮንታ ዞን ሥራና ክህሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ አደሮ በበኩላቸው በአካባቢው የሚገኘውን የቱሪዝም ጸጋ ለስራ ዕድል ለመጠቀም በቂ ግንዛቤ ያልነበረ መሆኑን ገልጸው፣ ለሶስት መቶ ሰው እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ከሶስት ወረዳና ሁለት ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ ናቸው ብለዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ በቅርብ ወራት ውስጥ ተጠናቀው ስራ የሚጀምሩ ፕሮጀክቶች ብዙ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማቅረብ ከማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ጋር በቀጣይነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው በምግብና መጠጥ መስተንግዶ፣ በቤት አያያዝና ላውንደሪ፣ በምግብ ዝግጅትና ሌሎችም የሙያ መስኮች ላይ ያተከረ ነው፡፡
ውድ የገጻችን ተከታዮች ላይክና ሼር በማድረግ መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን።
Recent Comments