በኮንታ ዞን በሆቴል ዘርፍ ለሶስት መቶ ወጣቶች እየተሰጠ የነበረው ተግባር ተኮር የአጭር ጊዜ ስልጠና ተጠናቀቀ።
በኮንታ ዞን የሚገኘውን የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ በሙያ የተደገፈ እንዲሆን ለማስቻል በሆቴል ዘርፍ ለሶስት መቶ ወጣቶች እየተሰጠ የነበረው ተግባር ተኮር የአጭር ጊዜ ስልጠና ተጠናቀቀ።
በዞኑ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በዘርፋ የሰለጠነ ብዙ የሰው ሀይል የሚያስፈልግ መሆኑን የገለጹት የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ደምሴ ቱሪዝም ማሰልጠኛ አንስቲትዩት በስልጠናና ሌሎች ስራዎች እያከናወነ ለሚገኘው ተግባር እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ በቀጣይነትም በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እና በማማከር ዘርፎች ከኢንስቲትዩቱ ጋር አብሮ መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው እየተሰጠበት ከሚገኙው መካከል የጪዳ ኮሌጅ ዲን አቶ ይርጋለም ሜታ በበኩላቸው ሰልጣኞች ስለዘርፉ መሰረታዊ እውቀት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ኮሌጁ በሆቴልና ቱሪዝም የሙያ መስኮች በጥቂት የሰው ሀይል ሰልጠና መስጠት መጀመሩን የገለጹት የኮሌጁ ዲን ጥሩ ተሞክሮዎች የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሰልጠናው ተሳታፊዎች ጥሩ አቀባበል እንደነበራቸው ኢንስትራክተር ብሩክ አዳሙ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን ከተከታተሉት መካከል ሄኖክ አባተ እና ዮሐንስ አሰፋ በሚገኘው የስራ ዕድል ለመጠቀም የሚያስችላቸው ስልጠና መሆኑን ገልጸው በአከባቢው እየመጣ ላለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችለናል ብለዋል፡፡ ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል፡፡
ኮንታ ዞን እንደ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፣ ገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት፣ በግሉ ዘርፍ እየለሙ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች፣ ቱባ ባህል፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች የሚገኙበት ነው፡፡

Recent Comments