ኢንስቲትዩቱ አሰራራቸውን ያጠናቸውን የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በካፒታል ሆቴልና ስፓ የባህላዊ ምግብ አዳራሽ ሜኑ በማካተት ለእንግዶቹ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነትና የሰነድ ርክክብ አደረገ።
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ያጠናቸውን በየክልሉ የሚገኙ የብሔር ብሔረሰብ የባህላዊ ምግቦች በካፒታል ሆቴልና ስፓ በመገኘት በባህላዊ ምግብ አዳራሹ ለእንግዶቹ ማቅረብ የሚያስችል ሰነድ በኢንስቲትዩቱ የምርምር እና ማማከር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ርክክብ ተደርጓል።
አቶ ይታሰብ ስዩም ካፒታል ሆቴልና ስፓ በከተማችን ከሚገኙ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች አንዱ መሆኑን ገልጸው ሆቴሉ ኢንስቲትዩቱ ያጠናቸውን ምግቦች ለተገልጋዩ ለማቅረብ ፍላጎቱን ማሳየቱን እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ በዚህ ረገድ ሆቴሉ ቀዳሚ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህ ተግባር ለቱሪዝም እድገት እና ለስራ እድል ፈጠራ ያለው ሚናም ጉልህ መሆኑን ጠቁመው ፣ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው ተብለዋል ።
የሆቴሉ ሥራአስኪያጅ አቶ ባንታየሁ ወ/ሚካኤል ኢንስቲትዩቱ ከነበረው ስምና ለኢንደስትሪው እድገት ማበርከት የሚጠበቅበት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ ጉልህ ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ ካሉ በኋላ በሆቴላቸው ኢትዮጵያን ሊገልጽ የሚችል ባህላዊ ምግብ ማቅረብ መቻላቸው ለተጠቃሚው ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የሆቴሉ ዋና ሸፍ እና ም/መ ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው ምግቡ የሚዘጋጅበት ጥሬ እቃ በቅርብ የሚገኝ እና ሀገርኛ ጣዕሙን እንደያዘ ለማቅረብ ከዶክመንቱ ባሻገር የባለሙያ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ምግቡ መዘጋጀቱ አንድ ቱሪስት ኢትዮጵያ መጥቶ ሌሎች ክልሎችን ማየት ባይችል በከተማው ባሉ ሆቴሎች የየክልሎቹን ባህላዊ ምግቦችና መጠጦችን ማግኘት እንዲችል ማድረግ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ባህላዊ ምግብ ቤቶች ላይ ከክትፎና ከዶሮ የዘለለ ምግብ እየቀረበ አለመሆኑን የገለጹት ባለሙያዎቹ ፤ አሁን ኢንስቲትዩቱ የባለሙያና የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በየክልሉ ያሉ በምግብ ዝግጅቱ የተሳተፉ የየብሔረሰቡ ባለሙያዎች ጭምር እንዳስፈላጊነቱ እገዛ የሚያደርጉበትን ሁኔታ እንደሚመቻች ም/ዋና ዳይሬክተሩ ቃል ገብተዋል። ሀገራችን ካላት የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ሀብቶች በተጨማሪ የምግብ ቱሪዝም ላይ ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ከተሰጠው ተልዕኮ በመነሳት ይህ ጅማሮ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ከተጠቃሚው እና ከሆቴሎች የሚገኙ ተጨማሪ አስተያየቶችን በመውሰድ ስራውን ከፍ ወደአለ ደረጃ አንደሚሸጋገር ተስፋቸውን ተናግረዋል። የባህላዊ ምግብ ዝግጅት ጥናት ሰነድ ርክክብም በሌሎች ሆቴሎች የሚቀጥል ይሆናል።
ትክክለኛ የተቋሙን መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/

Recent Comments