በትግራይ ክልል የሚገኘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ እንዲቻል በስልጠና፣ ምርምርና ማማከር በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከትግራይ ክልል ቱሪዝም ባለድርሻዎች ጋር በመሆን በክልሉ የሚገኘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ አብሮ መስራት በሚቻልባቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በኢንስቲትዩቱ በኩል ከክልሉ ጋር መስራት የሚቻልባቸውን ዘርፎች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ታደሰ ሞላ ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆቴልና ቱሪዝም ሙያዎች ብቃት ያለውን የሰው ሀይል ለማፍራት ፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ እንዲሁም በምክር አገልግሎት እያደረገ ያለውን ማብራሪያ ሰጥቷል።
ቱሪስቶችን ለመሳብ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ከመንግስት ቢሮዎች ጀምሮ ለሁሉም ቱሪዝም ባለድርሻዎች ስልጠናዎችን መስጠት በዘርፉ እየሰሩ ያሉ አካላትን የሚያነቃቃ መሆኑን የገለጹት በኢንስቲትዩቱ የአጫጭርና ተከታታይ ት/ት ክፍል ኃላፊ አቶ ግርማ ደቀባ በዘርፉ እየተተገበረ በሚገኘው ፖሊሲና ስትራቴጅዎችም ጭምር ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የትግራይ ክልል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የስራና ክህሎት ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም አረጋዊ የክልሉን ቱሪዝም ለማጠናከር ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሆን በአጭር፣ በመካከለኛና ረጅም ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎችን ዕቅድ በማዘጋጀት በተለይ በግበያ ትስስር ፣ ለዘርፉ ተዋናዮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እና የስልጠና ተቋማትን ለማደራጀት የግብዓት ድጋፎች የሚደረጉበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።
የሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት የወጣቶች ዘሊቂ ተጠቃሚነት ድርጅት (TYES) ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው የተጀመረው ውይይት የስራ እድልን ለመፍጠር በተለይም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ አስፈላጊውን በቅርበት የማስተባበር ስራውን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል ።
በውይይቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ተወካዮች፣ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ እና ሥራና ክህሎት ቢሮ ፣ የአስጎብኝ ድርጅቶች ማህበር ፣ የመቀሌ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ፣የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የክልሉ ሆቴሎች ማህበር እና ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት የወጣቶች ዘሊቂ ተጠቃሚነት ድርጅት (TYES) ተሳትፈዋል።
ትክክለኛ የተቋሙን መረጃዎች ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/