በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚያሰለጥኑ የቴክኒክና ሙያ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ተጀመረ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት (EASTRIP) ጋር በመተባበር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚያሰለጥኑ የቴክኒክና ሙያ መምህራን የንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡
ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢንስቲትዩቱ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ይህ ስልጠና ጥናት ላይ የተመሰረተና የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያማከለ መሆኑን ገልጸው ስልጠናው በሀገር ደረጃ ሰፊ የሥራ አድልን ለመፍጠርና ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ ሀብታሙ ክብረት በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ለሀገራት ልማት አስቻይ የኢኮኖሚ መሳሪያ ተደርጎ የሚወሰድ፤ ድህነትን ለማስወገድ፣ ሰላምንና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያ ተደርጎ ይታያል ብለዋል፡፡
ሀገራችን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ያላት ቢሆንም ዘርፉ ገና ያላደገና ተወዳዳሪ ያልሆነ በመሆኑ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስልጠና በመስጠት አስፈላጊ ነው፣ ይህን ችግር ለመቅረፍም የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ በአዲስ መልክ ሀገራዊ ተልዕኮ ተሰጥቶት በከፍተኛና በመካከለኛ ደረጃ በልዩ ሁኔታ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት(EASTRIP) በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከላት እየተተገበረ የሚገኝና በምስራቅ አፍሪካ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡
በስልጠናው ከአርባ አንድ ተቋማት የተወጣጡ አንድ መቶ ሰማንያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች የተሳተፉበት ሲሆን በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከተሞች የተግባር ስልጠናዎች እንደሚሰጡ የወጣው መርሐግብር ያመለክታል፡፡
ውድ የገጻችን ተከታዮች ላይክና ሼር በማድረግ መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን ።