በቢሾፍቱ ከተማ ለሆቴል ባለቤቶችና ባለሙያዎች በመስተንግዶ እና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ፣ ከቢሾፍቱ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ከኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር በቢሾፍቱ ከተማ ለሆቴል ባለቤቶችና ባለሙያዎች በመስተንግዶ እና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።
በስልጠናው መክፈቻ የተገኙት የኦሮሚያ ቱሪዝም ምክትል ኮሚሽነር ዶ/ር ምትኬ ቢተውልኝ እንደገለጹት ይህ ስልጠና በክልሉ ለሚከበረው ኤሬቻ በዓል የሚመጡ እንግዶችን የሚቀበሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ያስፈለገው እንግዶችን በአግባቡ እንድትቀበሉ እና እንድታስተናግዱ ነው ብለዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ ቱሪዝም ኮምሽን ኃላፊ አቶ ደጀኔ በጅሩ እንደገለጹት በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት ስልጠናና ማማከር መሰጠቱ በከተማው ለሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው፤ መንግስት ለቱሪዝም የሰጠውን ትኩረት እኛም በእቅዳችን በማካተት የሆቴል ኢንዱስትሪውን የሚመጥን ሙያተኞች በማፍራት አገልግሎት መስጠት መቻል እንዳለበት ተናግረዋል።
የሆቴል ባለቤቶችም ሆቴል መገንባት ብቻ ደንበኛ አያስገኝም አገልግሎቱን በማዘመን የተለያዩ ስልጠናዎችን ለባሙያዎች እንዲያገኙ እና ሆቴሉ በባለሙያ እንዲመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ስልጠናውን የሆቴል ባለሙያዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተክሉ ገ/ጊዮርጊስ እና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታሁን ደሳለኝ በመስተንግዶና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ሆቴሎች የተግባር ስልጠናና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በስልጠናው በቢሾፍቱ ከተማና ዙሪያ ከሚገኙ ሆቴሎች ከ1000 በላይ ባለሙያዎችና የሆቴል ባለቤቶች ተሳትፈዋል።
ይህ የማማከር ሙያዊ ድጋፍ በከተማው በሚገኙ ሆቴሎች እና መሰል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በየሆቴሎቹ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በጥናት በመለየትና በቦታው በመገኘት የማማከር አገልግሎቱ እንደሚቀጥል የኢንስቲትዩቱ የማማከር እና ማርኬቲንግ ዴስክ ሀላፊ አቶ ታምራት ተፈራ ገልፀዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/