የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ለመስጠት ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተዘጋጀ፡፡

ቱሪዝም ማሰጠልኛ ኢንስቲትዩት የዘርፉን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ለመስጠት የአስራ ሁለት ሙያዎች አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እና የሁለት መደበኛ ስልጠና ስርዓተ ትምህርት ክለሳ መደረጉን የኢንስቲትዩቱ ስልጠናና አቅም ግምባታ ዘርፍ ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዓለም ባንክ EASTRIP ፕሮጀክት ገንዘብ ድጋፍ ከዚህ በፊት ባካሄደው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መሰረት መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብታሙ ክብረት አሁን ስርዓተ ትምህርት እና የመማሪያ ሰነድ የተዘጋጀላቸው ሙያ መስኮች አዳዲስ በመሆናቸው የሥራ እድልን ለመፍጠርና አገልግሎትን ለማሻሻል ይረዳሉ ብለዋል፡፡
የአጫጭርና ማታ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ግርማ ደቀባ በበኩላቸው ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጀላቸው ሙያዎች ከዚህ በፊት ለብቻ ወጥቶ ስልጠና ያልተሰጠባቸው በመሆኑ በገበያ ላይ የሚፈለጉ ሙያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ስልጠና ወስዶ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ እንደ ጥሩ አማራጭ የሚሆኑ እንደሆነም አቶ ግርማ ደቀባ ገልጸዋል፡፡
ስርዓተ ትምህርት ከተዘጋጀላቸው ሙያዎች መካከል ከቋንቋዎች አረብኛ፣ ፍረንሳይኛና እንግሊዘኛ፣ የትኩስ መጠጥ አገልግሎት, ( barista service)፣ የመጠጥ አግልግሎት(bartender service)፣ የሥጋ ቤት አገልግሎት (Butchery), ጤናና ውበት(Wellness and Spa Service) እና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
በሰነድ ዝግጅት ላይ ሰላሳ አራት ሙያተኞች የተሳተፉበት ሲሆን የዓለም ባንክ EASTRIP ፕሮጀክት ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/