የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን ተገመገመ፡፡

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንሰቲትዩት በበጀቱ ዓመቱ በስልጠና፣ ጥናትና ምርምር እና ማማከር አገልግሎት ያከናወናቸውን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም በፌደራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተገመገመ፡፡
ለሱፐርቪዥን ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ተቋሙ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተደራሽ በሚሆን መልኩ በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር አና ማማከር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ እና በኢንተርፕራይዝ ልማት ደግሞ በላውንደሪ፣ዳቦና ኬክ ምርቶች ወደሥራ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
በሌላም በኩል በሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት በመኖሩ የአጫጭር ጊዜ ስልጠና ከፍተኛ ፍላጎት ያለ ቢሆንም የፍላጎቱን ያህል ለመስራት የቦታ ጥበት አንዱ ማነቆ እንደሆነባቸው ለሱፐር ቪዥን ቡድኑ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የስልጠና ቦታ ችግርን ለመፍታት በዓለም ባንክ ፕሮጀክት አዲስ ህንጻ ለመገንባት ከአማካሪ ድርጅት ጋር ውል መፈራረማቸውንም ገልጸዋል፡፡
የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ ገዛኸኝ አባተ የስልጠና ተደራሽነትን ለማስፋት በዘርፉ ስልጠና እየሰጡ ለሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት መምህራን አቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን እና ከባለድርሻ አካላት በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በበጀት ዓመቱ የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም የማማከር አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
የሱፕርቪዝን ቡድኑ ሰብሳቢ ዶ/ር በከር ሻሌ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ያለውን አቅምና እድሎች በሚገባ በመጠቀም ዓለም አቀፍ ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ይችላል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የራሱን ኢንተር ፕራይዝ መቋቋሙ ጥሩ ቢሆንም ኮር የሆኑ ሥራዎች በተለይ ኬተሪንግና ሁነት ሥራዎች ላይ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ማማከር አገልግሎቶች የተሰሩ ስራዎች ጥሩ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር በከር ሻሌ ዘርፉ በጣም ብዙ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶች የሚፈልግ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሱፐርቪዥን ቡድኑ በማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ሥራዎችን እና ወርክሾፖችን ተዟዙረው ተመልክተዋል ፡፡
@top fans #ፎሎ_በማድረግ_ቤተሰብ_ይሁኑ