በEASTRIP ፕሮጀክት እየተሩ የሚገኙ ስራዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ከኢንዱስትሪ ቴክኒካል አማካሪ ቦርድ ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በEASTRIP ፕሮጀክት በሶስተኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ ጊዜ ስራዎች ላይ ከኢንዱስትሪ ቴክኒካል አማካሪ ቦርድ አባላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በፕሮጀክቱ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በፕሮጀክቱ ገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የኢንስቲትዩቱ ሁለገብ ሕንጻ ከይዞታ ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር በመፈታቱ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የቅርብ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ድጋፍ የተሰሩት የጥናትና ምርምር ስራዎች ዘርፉን ለማሳደግ የሚጠቅሙ ናቸው፣ በተለይ ሀገር በቀል የባህል ምግቦች እውቀት ጥናት የባህል ምግቦች እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት እንዲሆን የሚያስችሉ እንዲሁም የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጥናቶቹን ውጤት ተደራሽ በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውል ከባለድርሻ አካላትና ክልሎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አፈጻጸሙን ያቀረቡት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አብርሃም ለገሰ በፕሮጀክቱ ገንዘብ ድጋፍ የቱሪዝምና ሆስፕታሊቲ ዘርፍ ሰው ሀይል ፍላጎትና አቅርቦት ጥናት፣ ለአሰልጣኞችና አስተዳደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን እና አዳዲስ የትምህርትና ስልጠና ሰነዶች ዝግጅትና በፕሮጀክቱ ገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው ሁለገብ ህንጻ ከዲዛይን አማካሪ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፈራረም የመጀመሪያ ዲዛይን መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ መልካሙ መኮንን በበኩላቸው ያለው አፈጻጸም ጥሩ መሆኑን አብራርተው የሚገነባው ሁለገብ ህንጻ ኢንስቲትዩቱ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራትና ለሚሰሩ ሆቴሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ ዲዛይኑ እንዲዘጋጅ እና እንዲገነባ ቦርዱ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የቦርዱ አባላት የተሰሩ ስራዎች ላይ እና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ እቅዶች ላይ ያላቸውን ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/