የዜጎችን የሥራ ፈጠራ ዕድልን ለማስፋት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ስልጠናዎችን ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአስራ ሰባት ሺህ ዜጎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት የሥራ እድልን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የቱሪዝም ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ተቋሙ በቀጣይ አምስት ወራት በልዩ ሁኔታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎች ዙሪያ ከሰላሳ ስድስት በላይ ከሚሆኑ በዘርፉ ከተሰማሩ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡ የምክክሩ ዓላማ ከክልሎች ጋር በመተባበር ዜጎች በአጫጭር ስልጠና የስራ እድልን የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማስፋት መሆኑን ተገልጸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀበታሙ ክብረት በበኩላቸው ሀገራችን በተለይም በባህላዊ ምግብ አሰራሮች እምቅ ሀብት ያላት ቢሆንም በግንዛቤ እጥረት ዜጎች በዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸው ይህን የክህሎትና ግንዛቤ ችግርን በትምህርትና ስልጠናዎች በመቅረፍ ዜጎች በቀላሉ የሥራ ዕድልን የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የሥራ እድልን ከመፍጠር ባለፈም ሀገር በቀል የምግብ ዝግጅት እውቀቶች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲሻገሩ ከክልሎች ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዕቅዱን ለማሳካት የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ጥናትና ምርምሮችን ፣ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠትና አስፈላጊውን የማስተባበር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከምክክሩ ተሳታፊዎች መካከል የደብረብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ኃላፊ አቶ ባሻዬ በየነ በበኩላቸው ዘርፉ ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩን ገልጸው የመምህራን አቅም ግምባታ፣ ዜጎች ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ከኢንስቲትዩቱ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰሩ አብራርቷል፡፡
የጅንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተወካይ አቶ መርዕድ በበኩላቸው በጂንካ ከተማ ካለው የቱሪስት ፍሰት አንጻር ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር አናሳ በመሆኑ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩና የዜጎችን የሥራ ዕድል ለማስፋት ኢንስቲትዩቱ ከተቋማቸው ጋር የተጀመሩ ሥራዎችን ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ተናግሯል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የቀጣይ አምስት ወራት ልዩ እቅድ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር፣ የባህላዊ ምግብ ዝግጅት ጥናት በአቶ አብይ ከበደ እና የአጫጭር ጊዜ ስልጠና አሰራር በአቶ ግርማ ደቀባ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡