“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት – ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ቃል በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ውይይት ተካሄደ

“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ቃል ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በወጣው የማስፈፀሚያ ሰነድ ላይ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም የገነት ሆቴል ሰራተኞች በገነት ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩ ዋንኛ ዓላማ እንደ ሀገር ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሰራተኛው የችግሩን አሰከፊነት በመገንዘብ የራሱን ሚና እንዲወጣ ማስቻል መሆኑ ታውቋል።
መድረኩን የከፈቱት የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደገለጹት እኛ ኢትዮጵያዊያን ምርታማ የሰው ኃይል፣ መልክዕ-ምድራዊ አቀማመጥና የተፈጥሮ ሀብት የታደልን መሆናችን በማስታወስ እነዚህን በአግባቡ አቀናጅተን እንደ ሀገር ከእርዳታ ጠባቂነትና ከተረጅነት መንፈስ መውጣት ይገባናል ብለዋል፡፡
በማህበረሰብ ደረጃ በችግር ጊዜ መረዳዳታችን የቆየ ሀገራዊ እሴታችንን በመጠበቅ፤ ዜጎች ከተረጅነት አስተሳሰብ ተላቀው ሰርተው ለመለወጥ እንዲችሉ በሚደረገው ንቅናቄ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የውይይቱን ሰነድ የተቋሙ ሥራ አመራርና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ አቀርበዋል።
የውይይት ሰነዱን ተከትሎ የተቋሙ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ተረጅነትና ልመና የግለሰብ፣ የማህበረሰብና የሀገርን ሁለንተናዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባርና አስተሳሰብ መሆኑን በመረዳት የአመለካከት ለውጥ ላይ በተደራጀ አግባብ በቅንጅት ልንሰራበት እንደሚገባ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/