ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ክልሎች እና ዞኖች ያጠናቸውን ባህላዊ ምግቦች በምግብ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት እና ለገበያ ለማቅረብ እንዲቻል ከሀይሌ ግራንድ ሆቴል ጋር የሰነድ ርክብክብ አካሄደ
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሲዳማ፣ የአፋር እና የሀረሪ፣ የጋምቤላ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ባህላዊ ምግቦችን በማጥናት በባለ ኮከብ ሆቴሎች በምግብ ዝርዝር እንዲገቡ በማድረግ ወደ ሀገራችን የሚመጡ የውጭ ጎብኝዎችም ሆኑ በሀገራችን ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ዜጎች ባህላዊ ምግቦችን በፈለጉት አካባቢ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ገልጸዋል።
እንዚህን ምግቦች በባለኮከብ ሆቴሎች በምግብ ዝርዝር ከማካተት ባሻገር ለሥራ እድል ፈጠራ እና ዘርፈ ብዙ ለሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅም ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሰነድ ርክብክብ ወቅት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት የሰነድ ዝግጀቱ በየክልሎቹ የሚገኙ የብሄሩ ተወላጅ እናቶች ጋር በመሄድ በተቋሙ ባለሙያዎች ተደግፎ የተሰራ ሲሆን፣ ሥራው ሲሰራ ከአንዱ ክልል፤ ወደ ሌላ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እሴት እየተጨመረበት መምጣቱን በመጠቆም በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በማካታት በሌሎች ክልሎችም ጥናቱ የሚካሄድ መሆኑን አሳውቀዋል።
የሀይሌ ግራንድ ሆቴል ዋና ስራአስኪያጅ አቶ እምሻው ተሾመ በበኩላቸው ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሀገራችን ባህል ትኩረት ተሰጥቶ ይህንን ሰነድ በማዘጋጀት ማቅረቡ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰው የሀይሌ ግራንድ ሆቴል በአዲስ መልክ ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት ቀድሞ ተቋሙ በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ እነዚህ የተለያዩ አከባቢ ባህላዊ ምግቦች በምግብ ዝርዝር ውስጥ ለማስገባት እንደተግዳሮት የሚነሳውን የግብዓት እጥረትና የክህሎት ክፍተቶች በተባለው ልክ ከተሟላ በሆቴላችን የበርካታ ክልል ምግቦች በምግብ ዝርዝራችን በማካተት ቀዳሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
አቶ ይታሰብም እነዚህን ባህላዊ የምግብ አይነቶችን ለማዘጋጀት ተግዳሮት የሚሆኑ የግብዓት ችግሮችን ከክልሎች ጋር ትስስር በመፍጠር ማሻሻል እንደሚቻልና የክህሎት ክፍተቶችን በማሰልጠኛው አሰልጣኞች ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የሆቴሉ የኦፐሬሽን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እጅጉ እንዳሻው በበኩላቸዉ ማሰልጠኛ ተቋሙ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው ሰነዱን ተቀብለው ሥራ ላይ ለማዋል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የመጀመሪያው ባህላዊ የምግብ ዝግጅት አሰራር ሰነድ እና ስምምነት በካፒታል ሆቴል መካሄዱንና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ በገነት ሆቴል በምግብ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ምግቦች ቅምሻ መደረጉ ይታወቃል።
ትክክለኛ የተቋሙን መረጃዎች ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et/

Recent Comments