ኢንስቲትዩት ከአማካሪ ቦረዱ ጋር መከረ።
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የ2017 ዓ.ም የሶስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም እና ኢንስቲትዩቱ ያጠናውን በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ስምሪት እና የገበያ ፍላጎት ለኢስትሪፕ(EASTRIP) ፕሮጀክት ቴክኒካል አማካሪ ቦርድ አቅርቦ ምክክር አካሄደ።
የምክክር መድረኩን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ሲከፍቱ እንደተናገሩት አማካሪ ቦርዱ ከተቋቋመ ጀምሮ በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ በትብብር ስልጠና፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሁም በሁሉም ሙያዊ ድጋፍ በሚያስፈልጉን ሁሉ ድጋፋችሁ አልተለየንም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም ኢንስቲትዩቱ ያሉትን የዘርፉን አሰልጣኞችና አማካሪ ቦረዱን በመጠቀም በዘርፉ የሚታየውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በአጫጭር ስልጠና ሥራ ያላገኙ የዩንቨርሲቲ ምሩቃንን ለማሰልጠን፣ ከአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የቱሪስት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ስልጠና ለመስጠት እና ከህፃናት አያያዝ ጋር የሚስተዋለውን የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል የሞግዚት ስልጠና በዚህ በጀት ዓመት ሊሠሩ የታቀዱ እንደሆኑ ገልጸዋል ።
የቴክኒካል አማካሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ መልካሙ መኮንን እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ እኛን በሚፈልግበት የትኛውም ጉዳይ ላይ ተገኝተን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ካሉ በኋላ በተለይ ተቋሙ ከመደበኛው ስልጠና ባሻገር በአጫጭር ሊሠራ ያቀዳቸውን ስልጠናዎች ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ያለው አስተዋጾ የጎላ ነው ብለዋል።
የኢስትሪፕ(EASTRIP) የሶስት ወር አፈፃፀም ሪፖርት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብርሃም ለገሰ ፤የጥናት ጽሑፉን ደግሞ የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ አቶ ይታሰብ ስዩም አቅርበዋል። የአማካሪ ቦርዱ ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም ከቱሪዝምና ሆቴል ማህበራት የተቀናጀ 11አባላት ያሉት ነው።
https://www.facebook.com/tticommunication
Recent Comments