የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በEASTRIP ፕሮጀክት እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ላይ ከኢንዱስትሪ ቴክኒካል አማካሪ ቦርድ ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽንና ቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት (EASTRIP) በ2015 በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች ሂደትን ለመገምገምና የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ከኢንዱስትሪ ቴክኒካል አማካሪ ቦርድ አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመጠቀም በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ይህን በአግባቡ ለመጠቀም የሰለጠነና ብቃት ያለው ሰው ሀይል ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የሀገራችንን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መርሃ ግብሮችን ተደራሽ ለማድረግ፣ ጥራትን ለማሻሻልና ስፔሻላይዜሽንን ለማጎልበት እንደሚረዳ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ቴክኒካል አማካሪ ቦርዱ ኢንስቲትዩቱ ከግል ዘርፉ ጋር የተጠናከረ ትስስር በመፍጠር የኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያሟላ የሰለጠነ ሰው ሀይል ለማቅረብና የትብብር ስልጠናዎች ላይ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አቶ ጌታቸው ነጋሽ ገልጸዋል፡፡
የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የሥራ አመራርና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ስራ ላይ እንዲውል የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማዘጋጀትና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞች፣ የኢንዱስትሪ አማካሪ ቦርድ አባላትና በዚህ ስራ ላይ ለተሰተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የተያዙ በማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች አፈጻጸም ለፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪዎች ቀርቦ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ግብረመልስ መሰጠቱን የገለጹት አቶ ገዛኸኝ አባተ ፕሮጀክቱ ኢንስቲትቱን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም ስለሚሆን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብሏል፡፡
የሀገራችንን ቱሪዝም ለማሳደግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ብቻ ማልማት በቂ ባለመሆኑ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ብቃት ያለው የሰው ሀይል እጥረት ችግር ለመፍታት ሊሰራ ይገባል ያሉት የቴክኒካል አማካሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ መልካሙ መኮንን ፕሮጀክቱ ይህን ለመለወጥ ትልቅ መሰረት ስለሚሆን ለዕቅዱ ስኬት እንሰራለን ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2016 ዕቅድ በማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አብሃም ለገሰ የቀረበ ሲሆን በፕሮጀክቱ ማዕቀፍ የተሰሩ ሶስት የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡
ውድ የገጻችን ተከታዮች ላይክና ሼር በማድረግ መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን ።