በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ተገቢውን ውጤት ለማምጣት በዘርፉ የሰለጠነና ብቁ የሰው ሃይል በብዛት ማሰማራት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በቱሪዝም መዳረሻዎችና ቱሪስት አገልግሎት ደረጃ ያሟሉ ሆቴሎች በሰው ሃይል ፍላጎትና አቅርቦት በኩል ያላቸውን ገጽታ ለማሳየት በቀረበ ጥናት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ መክሯል።

በዚሁ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደተናገሩት፤ የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ ፍሰት ለማረጋገጥ የሰለጠነና ብቃቱ የተመዘነ ባለሙያ ማሰማራት ወሳኝ ነው፡፡

እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ ነባሮቹን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማደስ እና አዳዲሶቹንም በስፋት ለመገንባት የሰው ሃይል ላይ መስራት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ በጥናት የተደገፈ ስራ ማስፈለጉንም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ችግር ፈቺ ጥናቶችን ወደ ተግባር በመቀየር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ የሚጨምሩ አሰራሮችን በመከተል ዘርፉን የማሻሻል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ተፈጻሚነት የቱሪዝምና ሆቴል ማሰልጠኛዎች የተሟላ ስልጠና በመስጠት ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራትና በዘርፉ በማሰማራት በኩል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አሰልጣኝና ተመራማሪ አቶ ፍሬው አበበ በሰው ሃይል ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ባቀረቡት ጥናት ከተዳሰሱት 401 ሆቴሎች 47 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በሰለጠኑና የብቃት ምዘናን ባሟሉ ባለሙያዎች እየሰሩ መሆኑን አሳይተዋል፡፡

ብቁ ባልሆነ የሰው ሃይል የሚያሰሩ አካላትም ከትርፍ ይልቅ ባልተሟላ አገልግሎታቸው ምክንያት ደንበኛ ሲሸሻቸው መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም በዘርፉ የተመረቁትም ቢሆኑ የክህሎት ክፍተት እንደሚታይባቸው አስረድተዋል፡፡

ይህ ጥናት ለሆቴሎችና ቱሪዝም መዳረሻዎች ክፍቶቻቸውን በመጠቆም ብቃት ባለው ሰው ሃይል ልማት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ አጋዥ የሚሆን ነው ሲሉም አቶ ፍሬም ተናግረዋል ፡፡

የሰለጠነ የሰው ሃይል በብዛት ለማሰማራትም ደረጃቸውን የጠበቁ የማሰልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋትና የባለድርሻ አካላት ትብብር ችግሩን መፍታት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባው ኢኮኖሚያዊ እድገት የባለሙያ ጥራት እንዲሁም የሀገር ገጽታን ለውጥ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡