(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ የካቲት 01/2017 ዓ.ም ቢሾፍቱ) ‘‘ሥነምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት’’ በሚል መሪ ቃል ለሥራ እና ክህሎት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች የሥነምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡በስልጠናው የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) አገልግሎት አሰጣጣችን ለማዘመን እና ዜጎች የሚረኩበት አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የአመራሩ ሚና የጎላ በመሆኑ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ስልጠናው በተቋማችን ውስጥ ብልሹ አሰራሮችን አስቀድሞ ለመከላከል የተሻለ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።የስልጠናው ዋና አላማ በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በመታገል ረገድ፤ አመራሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው በማድረግ ከሙስና የፀዳ ተቋማዊ አሰራር እንዲኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።
ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል በዘርፉ የሚስተዋለውን የሙስና አዝማሚያ በመቅረፍ ተቋማዊ ተልኮውን መወጣት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በተቋሙ በክህሎት ልማት፣ አሰሪና ሰራተኛ እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ ላይ ለዜጎች አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን ለሙስና እና ብልሹ አሰራር ተጋላጭነት በመሆኑ፣ ከዜጎች ጋር ቀጥተኛ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ቀልጣፋ ፣ ግልፅ እና ፈጣን ለውጥ ማምጣት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል።
ስልጠናው በሙስና እና ብልሹ አሰራር ፅንሰ ሀሳብ፣ የሙስና ምንነቶች፣ ዘርፉ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር ተጋላጭነት ላይ ትኩረት አድርጎ በዶ/ር ሱሌማን ሽኩር እና ዶ/ር አበበ አስረስ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፥ በቀጣይም ለሠራተኛው የሚሰጥ ይሆናል።
ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!
Recent Comments