ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ኢ መስከረም 08/ 2012 ዓ.ም
ተግባርን መሰረት ያደረገ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም መምህራን የመስክ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት መስክ የስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ፤ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማድረግ የመምህራን እውቀትና ክህሎት እንዲዳብር እንዲሁም አስፈላጊው የመማር ማስተማር ግብዓቶችን ማሟላት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ስለሆነም ኢንስቲትዩቱም አስፈላጊ የስልጠና ግብዓቶችን ከማሟላት ጎን ለጎን የመምህራንን አቅም ለማጎልበት በክረምቱ ወቅት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ይህ የቱሪዝም ዘርፍ መምህራን የተግባር ስልጠና በንድፈሀሳብ ደረጃ የአጭር ጊዜ ስልጠና ሲሰጥባቸው የነበሩ ርዕሰ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ከመስከረም 02 /2012 ዓ.ም ጀምሮ በአፋር ክልል በሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ የመስክ ጉብኝት በአካባቢው የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ዙሪያ ተጨማሪ ግንዛቤን ለማስጨበጥና ለጥናትና ምርምር መነሻ የሚሆኑ ዳሰሳዎች የተደረገበት ነው፡፡
ጉብኝቱ የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎች መገኛ በሆነው በዝዋይ ሀይቅ፣በአዋሽ ፓርክ፤ የአዋሽ ወንዝ የመጨረሻ መዳራሻ አካል በሆነው በገመሪ (ቀመሪ) ሀይቅ፤ በዓለም ልዩ በሆነው የኤርታአሌ እሳተ ጎመራ እንዲሁም በዓለም ከባህር ወለል በታች 116 ሜትር በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው የዳሎል ዝቅተኛ ቦታዎችን በትኩረት ተጎብኝተዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት መምህር ማሩ እማኙ እንደገለጹት በንድፈ ሀሳብ የሚገኘውና በአካል በቦታው በመገኘት የሚሰጥ ትምህርት እኩል አይደልም፤ በተለይም የቱሪዝም ትምህርት በጣም ሰፊና ከብዙ እውቀቶች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በየወቅቱ በተለያዩ ስልጠናዎች መምህራንን ማብቃት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ትምህርታዊ ጉዞ የተደረገባቸው መዳረሻዎች ከዚህ በፊት በመምህራኑ ያልተጎበኙ በመሆናቸው ተጨማሪ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
መምህር ሞሲሳ ንጉሴም በበኩላቸው ይህ የአቅም ማጎልበቻ የተግባር ስልጠና ተጨማሪ ትምህርትን ያገኘንበት በመሆኑ ወቅታዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ሁኔታን መሰረት በማድረግ የተጎበኙ ቦታዎችንም ጭምር በማስረጃ በተደገፈ መልኩ ስልጠና ለመስጠት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ከቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አካባቢዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ያለመኖር፤ የመሰረተ ልማት ችግሮች(መንገድ)፣ አንዳንድ የመዳረሻ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ችግር፣የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንዳንድ መዳረሻዎች ላይ ያለመኖር (ባንክ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ…)፣ የአስጎብኝ ባለሙያዎች ብቃት እንዲሁም ስለቅርሶችና መዳረሻ ቦታዎች በቂ ግንዛቤ ያለመኖር ችግሮች እንዳሉ መታዘባቸውን የቱሪዝም ባለሙያው ማሩ እማኙ ገልጸዋል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለአካባቢ አስጎብኝዎች በአጫጭርና በተለያዩ የስልጠና መርሐግብሮች በማሳተፍ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት እንዳለበት መምህራኑ ጠቁመዋል፡፡ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የቅርሶችና ፓርኮች አያያዝ ጋር እንዲሁም የመሰረተ ልማትን ከማሟላት አንጻር ያሉ ችግሮችን ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለበት እንላለን፡፡
በብሩክ ታደሰ
Recent Comments