ቱ.ማ.ኢ መጋቢት 23 /2017 ዓ.ም
አንጋፋዎቹ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና ጎንደር ዩኒቨርስቲ በጥናትና ምርምር ፣ በስልጠና እና በማማከር አገልግሎት አብሮ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ ።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ሁለቱ ተቋማት ያደረጉት ስምምነት በቱሪዝም ዘርፍ ከስልጠናና ከምርምር ባሻገር ለፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ተቋማቱ ከስምምነቱ በኋላ የድርጊት መርሐግብር በማዘጋጀት ወደተግባር እንደሚገቡ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን በመስጠት በአካባቢው እየለሙ ያሉ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም ጭምር ለማጠናከር በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን(ዶ/ር) በበኩላቸው ጎንደር ዩኒቨርስቲ ትልቅ ትኩረት ከሚሰጥባቸው የስልጠና ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ በመሆኑ ከዚህ አንጋፋ ተቋም ጋር ስንሰራ ትላልቅ እቅዶችን ማሳካት እንችላለን ብለዋል።
ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ለዩኒቨርስቲው ትልቅ አጋር ይሆናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዘርፉ ላይ ተደቅኖ የነበረውን ችግር እንዲቀረፍ እና በክልሉ ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ሁሉቱ ተቋማት አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል ።
የኢንስቲትዩቱ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም በበኩላቸው የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ፕሮጀክቶች የሚገኙበት በመሆኑ ክልሉ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማጠናከር ከሰሞኑ በሆቴሎችና በአስጎብኝ ድርጅቶች ስልጠናዎችና የማማከር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው ፤ ከዩኒቨርስቲው ጋር በመተባበር በግንቦት ወር ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
የአስተዳደርና ሥራ አመራር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት ሲቀናጁ ካላቸው ልምድ አንጻር ትልቅ ሥራ ለመስራት የሚያግዝ በመሆኑ አብሮ ለመስራት ዩኒቨርስቲው ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎችን ይጠቀሙ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/tticommunication
ቴሌግራም ፡https://t.me/tticommunication
ዌብሳይት፡ https://www.tti.edu.et

Recent Comments