ቱ.ማ.ኢ. ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጋር አጭር ቆይታ

አንጋፋው የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል በአዲስ አደረጃጀት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መባሉ ተቋሙ ለረዥም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረውን ጥያቄ የመለሰ ነው ሲሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ገለጹ፡፡
ተቋሙ ከተቋቋመበት ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተብሎ ስልጠና ሲሰጥ የቆየው ይህ ተቋም ከ2002 ዓ.ም በኋላ የደንብ ማሻሻያ ተደርጎለት ከኢንስቲትዩት ወደ ማዕከል ዝቅ ብሎ ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ማዕቀፍ እስከ ደረጃ አምስት በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ይህ ደንብ ተቋሙ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች እና ለዘርፉ ካለው አንጋንፋነት ጋር ሥራውን አሳድጎ ለመሄድ አመቺ ባለመሆኑ በዘርፉ ባለሙያዎችና ተመድበው በሚመጡ የስራ ኃለፊዎች በየጊዜው የደንቡ ይሻሻልልን ጥያቄ ዛሬ ላይ ምላሽ ማግኘቱ ለተቋሙ ማህበረሰብም ሆነ ለዘርፉ ባለሙያዎች ትልቅ ደስታ እንደሆነ ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ከተጠሪነት አንፃር ሲታይ ላለፉት 53 ዓመታት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በወቅቱ ከነበረ የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ኮሚሽን ተጠሪ ሆኖ የቀጠለ ነበር፡፡ ሆኖም በአሁኑ አደረጃጀት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ውስጥ የገባበት ዋና ዓላማ በሀገራችን የሚታየውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በተለያዩ የአጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት ሥራን ከሰራተኛ ጋር ለማገናኘት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ቱሪዝም በባህሪው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወደስራ ማሰማራት የሚያስችል ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ በመሆኑ አገራችን ካላት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች፤ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠቀም ዘርፉን ለማልማትና ወጣቱም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን የማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ አሁን ባለው አደረጃጀትም ከዚህ ቀደም የሚሰጣቸውን የስልጠና የምርምርና የማማከር አገልግሎት በሰፊው ይሰጣል፡፡ ተቋሙ ብዙ ልምድ ባላቸው መምህራን የታገዘ እና 25 ያህል ቤተሙከራዎች እንዲሁም ገነት ሆቴልን ጨምሮ ልምድ የሚገኝበት ተቋም በመሆኑ ሌሎች በቱሪዝምና ሆቴል ስልጠና ለሚሰጡ ተቋማትም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት በጋራ ለመስራት ይደረግ የነበረውን እንግልት በመቀነስ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር አብሮ በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሥር መካተቱ ለተቋሙ የተሻለ እንደሆነ ዋና ዳሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየራሳቸው በሚኒስቴር ደረጃ መውጣታቸው ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው ከኛ ተቋም ጋር ደግሞ አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ ስራዎች እንዳሉን እና የአስር ዓመት ዕቅዳችንም ሆነ በርካታ ስራዎች በጋራ ስምምነት በመፈራረም አብረን የምንሰራው ሥራ እንደሚኖር መገንዘብ አለብን ብለዋል፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት የነበረውን ስያሜ መቀየርም ግርታ ሊፈጥርልን አይገባም፡፡ ሆቴል ማለት በቱሪዝም ውስጥ የሚካተት አንዱ ዘርፍ እንደሆነ መረዳት እንደሚገባ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በመጨረሻም የተቋሙ መምህራንና ሰራተኞች በሆቴልም በቱሪዝምም ብዙ ልምድ ያላቸው እና ብዙ ሀገራዊ ገዳዮችን ሲያሳኩ የቆዩ በመሆናቸው ሰልጣኞችን ከተቀጣሪነት ይልቅ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ሥራና ሰራተኛን ለማገናኘት ከዚህ በፊት ከነበረው ብርታት ይልቅ በስነ-ልቦናም ሆነ በአካል ዝግጁ ሆኖ መሥራት እንደሚጠበቅብንም በማሳሰብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡