— May 14, 2023 add comment በኢትዮጵያ ለቱሪስት መስህብነት የሚሆኑ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎች በእጅጉ በርካታ ናቸው።

ሀገሪቱ የሰው ዘር መገኛ ምድር ከመሆኗ አንፃር በእጅጉ ሲበዛ የአስደናቂ ቅርስ ሃብቶች ባለቤት መሆኗ ያን ያህል አስገራሚ አይሆንም።
ሀገሪቱ የእነዚህ ሁሉ ጸጋዎች ባለቤት ብትሆንም፣ በአለማችን ላይ በጎብኚዎች መዳረሻነት ከሚታወቁት አገራት ተርታ መሰለፍ አልቻለችም። በባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ እሴቶቿ በብዙ እጥፍ የምታስከነዳቸው አገራት ሃብቶቻቸውን የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና ምቹ መሰረተ ልማት የመገንባት፣ የመንከባከብ ተግባር በመስራታቸው ብቻ ቱሪዝምን የኢኮኖሚያቸው አንቀሳቃሽና የጀርባ አጥንት ማድረግ ችለዋል።
በተለይ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ቆይታ እንዳያራዝሙ፤ ይዘው የመጡትን ገንዘብ መልሰው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ ከሚያስገድዱ በርካታ ምክንያቶች አንዱ በዘርፉ ላይ የተሰማሩት ባለሙያዎችና የአገልግሎት ጥራት መጓደል አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሰማሩ የሆቴል ሙያተኞች፣ የአስጎብኚዎችና የሌሎች በተያያዥ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ብቃት፣ የአገልጋይነት ስሜት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።
ባለሙያው ኢትዮጵያ ስላሏት የቱሪስት መዳረሻዎች፣ መስህቦች እና ሌሎችም አስፈላጊ መረጃዎችን በበቂና ሳቢ በሆነ መልኩ ለጎብኚዎች ማድረስ የማይችሉ መሆናቸው የቱሪስቶች የመቆየት ፍላጎትን የሚቀንስ ሌላኛው አመክንዮ መሆኑን እነዚሁ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። እንደ ዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጥናትም ይህ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡ ቱሪስቶች ይዘው የመጡትን ዶላር አብዛኛውን መልሰው ከሚሄዱበት ምክንያት እንደሚመደብ ነው የሚጠቁመው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታውን ለማጉላት ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻነቷን ሊያረጋግጡ ከሚችሉት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት እየተተገበሩ የሚገኙት የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እንዲሁም በቅርቡ ወደ ትግበራ የሚገባው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የሚል ስያሜ ያላቸው ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለመገንባትና ዓለም አቀፍ ትኩረትን በዘርፉ ለመሳብ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጎን ለጎን የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማምጣት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይታመናል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በመሰረተ ልማት ረገድ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥሩ የቱሪዝም ዘርፉ ባለሙያዎች አረጋግጠው፣ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ግን በበቂና በሰለጠነ የዘርፉ የሰው ሃይል መመራት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስቸግር ጠቅሰው፣ ከቱሪዝም መዳረሻ ልማት ግንባታዎች እኩል የሰለጠነና ብቁ ባለሙያ የማፍራት ስራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይጠቀማሉ።
አቶ ይታሰብ ስዩም የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ግንባታዎች ጎን ለጎን በዘርፉ በሚሰማራው ብቁ የሰው ሃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ለዚህም የፖሊ ቴክኒክ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መሰል የቱሪዝም ሙያ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ትኩረታቸውን በዘርፉ የሰው ሀይል ልማት አድርገው የሚሰሩ አካላት ሊወስዱ የሚገባቸውን ድርሻና እርሳቸው የሚመሩት ኢንስቲቲዩት እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር አመልክተዋል።
“የሰለጠነ የሰው ሃይል ለቱሪዝም ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አስፈላጊና የጀርባ አጥንት ነው” የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ በተለይ የቱሪዝምና መስተንግዶው (የሆስፒታሊቲው) ዘርፍ ከሌላው ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ለዘርፉ ያለው ፍላጎት እና ክህሎቱ ከፍተኛ የሆነ፣ በስነ ምግባር የሚወደስ፣ በሚገባ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንደሚፈልግ ይገልፃሉ። ዘርፉ መልካም አቀባበልና መስተንግዶን (ሆስፒታሊቲ) እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ ይህም የሙያ ደረጃው ከፍ ያለ የሰው ሃይል ማፍራት ስራን መጠየቁን ያመለክታሉ። ከታላላቆቹ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና መሰረተ ልማት ግንባታዎች እኩል የሰው ሃይል የማፍራት ተግባሩ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
“በዘርፉ ያለው የሰው ሃይል ውስን እንደሆነ ተቋማችን በተለያየ ጊዜ በሰራቸው ጥናቶች አረጋግጧል”የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በመሆኑም በሂደት በቱሪዝም፣ በሆቴልም ሆነ በሌሎች መሰል ሙያዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ይህ ሲሆን አዲስ እየተገነቡ ያሉት እንደ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ወንጪ ደንዲና ሌሎችን ነባርና አዲስ መዳረሻዎች ላይ ብቁና ለዘርፉ የሚመጥን ባለሙያ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ መዳረሻ እንዲያደርጉ ብሎም ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ጉልህ ድርሻ ይጫወታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው ግብ መዳረሻዎችን መገንባትና ማልማት ብቻ ሳይሆን ከብቁና ውጤታማ ባለሙያ ጋር አስተሳስሮ የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪ ማድረግ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡
“ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ የተፈጥሮና የታሪክ አያሌ የቱሪዝም መዳረሻ ሃብቶች ያሉባት አገር ነች” የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ በዋናነት የሚነሳው ግን የመሰረተ ልማትና የሰለጠነ የሰው ሃይል ችግር እንደሆነ ይገልፃሉ። በመሆኑም በተለይ የሰለጠነ የሰው ሃይል በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ አግባብ በማሰልጠን ወደ ዘርፉ መቀላቀል አለበት የሚል የጋራ አቋም እንደ አገርም ሆነ የትምህርት ተቋማቱን በሚመሩት አካላት እንደተያዘም አቶ ይታሰብ ይጠቁማሉ።
በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት ባሻገር መንግሥት እየሰራቸው በሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች (ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ እና ሌሎችም) ላይ ተቀጥሮ መስራት ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጭምር ኢንስቲቲዩቱ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ተቋሙ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚሰራ ገልጸው፣ በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በአገሪቱ የሚገኙ ከ70 በላይ የሚሆኑ በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ የሚያሰለጥኑ የትምህርት ተቋማትን በአቅም ገንባታ እየደገፈ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
“ኢንዱስትሪው በጣም ከፍተኛ የሰው ሃይል የመሸከምና የስራ እድል የመፍጠር አቅም አለው” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተካሄደ ጥናት አሁን በዘርፉ ያለው ባለሙያ አቅም 30 በመቶ እንደሆነ የሚያመላክት መረጃ መገኘቱን ይናገራሉ። ይህን አቅም አሁን የሚገነቡትን ታላላቅ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በነባርና በአዲስ የመስህብ ስፍራዎች ውስጥ በቀጣይ አምስት ዓመታት ወደ 70 በመቶ የማሳደግ ግብ መቀመጡን ይገልፃሉ። ይህ የስራ እድል ፈጠራውን ከማሳደጉም በላይ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ነው ያመለከቱት።
አዳዲስ እየለሙ ባሉትም ሆነ በነባር የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቶች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ወጥና ተመሳሳይ ደረጃ ያለው ሙያዊ ብቃት እንደሌላቸው ይነገራል። ይሄም ጎብኚዎች የተዛባና የተደበላለቀ መረጃ፣ አገልግሎት እንዲሁም የእርካታ ደረጃን እንዲያገኙ ያስገደደ እንደሆነም ይገለጻል። ከዚህ አንፃር የትምህርት ተቋማት ባለሙያዎችን በሚያሰለጥኑበት ወቅት ተመሳሳይ ሙያዊ ብቃትና ክህሎትን ቀስመው እንዲወጡ ስርዓተ ትምህርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን አቶ ይታሰብ ይገልጻሉ።
ስልጠናዎች ተግባር ተኮር እንዲሆኑና ከኢንዱስትሪው ጋር በቅንጅት የሚሰጠብት አግባብ እየተመቻቸ እንደሆነ ይናገራሉ። በምሳሌነትም ኢንስቲቲዩቱ 70 ከሚደርሱ የዘርፉ ሆቴሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮች እንዲሁም የዘርፉ አንቀሳቃኞች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ተግባር ተኮር ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ይገልፃሉ። ይህንን ተሞክሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግስት ሃብት በማሰባሰብ የጀመራቸውና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራሉ ተብለው የሚታሰቡት የገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገርና ገበታ ለትውልድ እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ በሚፈለገው ብቁ ባለሙያ እንዲመሩ የግድ ይላል። ከዚህ አንፃር ምን አይነት ዝግጁነት ያስፈልጋል? የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው።
እነዚህን ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሲናገሩ ‹‹ እነዚህ የመዳረሻ ልማት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ አንዳንዶቹ በመንግሥት የሚያዙ አንዳንዶቹ ደግሞ በግሉ ዘርፍ የሚመሩ ናቸው›› ሲሉ ገልጸው፣ የትምህርትና ሙያ ስልጠናውም በዚሁ አግባብ የሚቀጥል እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ ከመንግሥት አንፃር በመላው አገሪቱ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊ ቴክኒክ ተቋማትና ኮሌጆች ብቁ ባለሙያን በተመረጡና እንደየ አካባቢያቸው ፀጋና ሃብት እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ ዘርፎች (እንደ ሆቴልና ቱሪዝም አይነት) ብቃት ያለው ሰልጣኝ እንዲያወጡና ሙያዊ ትምህርት እንዲሰጡ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ። ከዚህ መነሻ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዘርፉ የሚፈልገውን ሙያዊ ብቃትና ክህሎት የሚይዙ ባለሙያዎች እንደሚፈጠሩም ይጠቁማሉ።
“ስልጠናዎቻችን ዝም ብሎ እያስተማሩ ማስመረቅ መሆን የለባቸውም” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጥራት ላይ ያተኮረ፣ ያሉትንና የሚመጡትን እድሎች ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥና ውጤታማ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ በሙያው ስልጠና የሚሰጡ 70 የሚደርሱ ፖሊ ቴክኒክ ተቋማት፣ በርካታ የግል ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች 28 የሚደርሱ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህንን ታሳቢ አድርገው መስራት እንደሚኖርባቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ይህ አካሄድ ተግባር ላይ መዋል ከቻለም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አዳዲስ የሚሰሩትን የመዳረሻ ልማቶች ጨምሮ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሙላት የሚችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚቻል ገልፀዋል።
“የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል የምርምርና የፖሊሲ ግብአት ማቅረብ የሚለው ይገኝበታል” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቅርቡ ከምርምር ስራ አንፃር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። በተለይ ጥራትና ክህሎት ያለው በሙያ ስነ ምግባሩ የተመሰገነና የአገልጋይነት ስሜት የተላበሰ ባለሙያ ከማፍራት አንፃር ያሉትን ክፍተቶች በሳይንሳዊ ዘዴ የመለየት ስራ መሰራቱን ነግረውናል።
በመንግሥት ቁርጠኝነት እየተሰሩ የሚገኙ የቱሪዝም የመዳረሻዎች የሚፈጥሩትን የስራ እድል፣ የኢኮኖሚ መነቃቃትና አገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ እድል በተመሳሳይ በምርምርና በጥናት እንዲመለሱ ማደረጋቸንም ገልፃውልናል። ከዚህ ጋር በተገናኘ ኢንስቲትዩቱ ፕሮጀክቶቹ የሚፈልጉትን የሰው ሃይልና ሙያዊ ደረጃን በማመላከት ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ የማመላከትና ምክረ ሃሳብ የመስጠት ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015