ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹በሀገሬ ምርት እኮራለሁ፤ ከሀገር ውስጥ አምራቾች እገዛለሁ!›› በሚል መሪ ቃል ከ240 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር አዘጋጅቷል፡፡

ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በማስመልከትም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለፁት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከሚያደርጋቸው መንግስታዊ ድጋፎች አንዱ የገበያ ትስስር መፍጠር በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ተዘጋጅቷል፡፡
ከጥር 4 እስከ 9 ቀን 2015ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በሚካሄደው ኤግዚቢሽን እና ባዛር 246 ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉ ሲሆን ከ35 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍል ኤግዚቢሽን እና ባዛሩን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 600 ለሚሆኑ ጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 18 ሚሊዮን ብር ያህል የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም ማስተዋወቅ እና ኢንተርፕራይዞች ሥራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ሀብት እንዲፈጥሩ ዕድሎችን ማመቻቸት የኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ዋና ዓላማ መሆኑን ክቡር ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለስድስት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቢሽን እና ባዛር የገበያን ትስስር መፍጠርን ብቻ ሳይሆን የኢንተርፕራይዞችን ችግር መፍታትን ታሳቢ ያደረገ እና ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ጥናትና ምርምሮች የሚቀርቡበት የፓናል ውይይት የሚደረግበት ይሆናል፡፡
ተቋሙ በሚኒስቴር ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን እና ባዛር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ ክልላዊ መንግስት የሥራ፣ ክህሎት እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ነው፡፡
ጥር 2/2015 ዓ.ም፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊን ትኩስ የሥራና ክህሎት መረጃዎች ቴሌግራም፦https://t.me/fdre_mols በመወዳጀት ይከታተሉን::