” የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በቱሪዝም ዘርፍ የትምህርት ደረጃውን በማሳደግ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ሲሆን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት መድቧል ”

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንስቲትዩት 9ኛውን አገር አቀፍ የቱሪዝም እና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ማካሄድ ጀምሯል።
ቱሪዝም በፍኖተ ብልፅግናው ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት ግድ በመሆኑ ከሚያከናውናቸው የለውጥ ስራዎች መካከል የትምህርት ደረጃውን እስከ ደረጃ 8 ከፍ ማድረግ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰረተ ልማቱን ለማሟላትም 15ሚሊዮን ዶላር ሀብት መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ይህም ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
አገርን ለማሳደግ በመንግስት የሚደረጉ ጥረቶች ብቻ በቂ ባለመሆናቸው የግሉ ዘርፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማገዝ ተቋማት ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ሲሄዱ በራቸውን ክፍት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
አንጋፋው የቱሪዝም ኢንስቲትዩት ” ቱሪዝም ለአብሮነት” በሚል ትልቅ ትርጉም ያለው የሚያገናኝ ሳምንት በማዘጋጀቱ አመስግነዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክብርት ሚኒስትሯ አማካኝነት በቂርቆስ ክፍለከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የማዕድ ማጋራት በማከናወን የቀለብ ድጋፍ አድርጓል።
የቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት በበኩላቸው ዘጠነኛው የቱሪዝም እና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ተቋሙ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ሆኖ ወደ ኢንስቲትዩትነት ከፍ ያለበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ካሉ በኃላ በቱሪዝም ዘርፍ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል 33በመቶ ብቻ በመሆኑ ይህንን በ10ዓመቱ የልማት ዕቅድ ወደ 66 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቱሪዝም ሳምንቱ ቀጣሪና ተቀጣሪ የሚገናኝባቸው መድረኮች ፣ ዓውደርዕዮች፣ የምክክር መድረኮች፣ የሰልጣኞች ውድድር እና ሌሎችም ስነስርዓቶች እንደሚካሄዱበት ተገልጿል።