ቱ.ማ.ኢ. ህዳር 28/2016 ዓ.ም ቱሪዝምና የሚዲያ ሚና በሚል ርዕስ ወርሃዊው የቱሪዝም መሪዎች ወግ በቱሪዝም ሙያ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የውይይት መድረኩን አቶ ይታሰብ ስዩም የኢንስቲትዩቱ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ሲከፍቱ እንደተናገሩት በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶችና የመንግስት አካላት በየወሩ በተመረጡ ርዕሶች ዙሪያ እየተገናኙ ዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን እንዲለዩ ፣በጋራ መፍትሔ እንዲያመጡ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ከዚህ ቀደም በነበሩት መድረኮች የተገኙ ግብዓቶችን እንደ መነሻ በመውሰድ ተቋሙ ባለሙያዎቹን ተጠቅሞ የምርምር ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ሶስተኛው የቱሪዝም መሪዎች ወግ ልምዳቸውን እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉ እንደ ሀገር ያለበትን ተግዳሮትና ሚዲያው ላይ ባለመስራታችን እያጣነው ያለውን ገቢ ከሌሎች ሃገራት ተሞከሮ በማጣቀስ የውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ የቱሪዝም ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም አቅርቧል፡፡
ሄኖክ በመነሻ ጽሁፉ እንደገለጸው በሃገራችን የቱሪዝም ሃብት እና በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ከተመዘገቡ ቅርሶች አንፃር በአፍሪካ አንደኛ መሆናችንን ነገር ግን በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ በአግባቡ አለመጠቀማችን፣ ከቋንቋ አጠቃቀምና ስብጥር አንፃር ያለብንን ውሱንነት፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ የሚዲያ ተቋማት ቱሪዝምን አጀንዳ አድርጎ ለመስራት ፍላጎት አለመኖር፣ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በቂ የስልጠና ለማግኘት በዘርፉ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ነገር ግን ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት አድርገው ቱሪዝሙ ላይ እንሩንዲሰሩ የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረበው ርዕስ ዙሪያ ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወርሃዊው የቱሪዝም መሪዎች ወግ በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው መስተንግዶ እንዴት ማምጣት እንችላለን፤ሁለተኛው ዙር ሀገር በቀል እውቀቶችን እንዴት እናስፋቸው የሚሉ የመነሻ ርዕሶች ቀርበው ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡
ውድ የገጻችን ተከታዮች ላይክና ሼር በማድረግ መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንጠይቃለን።
Recent Comments