በስፔን ማድሪድ እየተካሄደ ባለው በ24 ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ተገለጸ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ከ170 የቱሪዝም መንደሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ መመረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የቱሪዝም ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ የወንጪ ሃይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው ባለው የተለየና ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑም ተገልጿል፡፡የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች አካላት ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ ለመመረጥ እንዲበቃ የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ በመንከባከባቸውም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የወንጪ ሐይቅ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆንና የበለጠ ለመሥራት እንደሚያነሳሳም ሚኒስትሯ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ በስፔኗ ዋና ከተማ ትናንት የተጀመረው 24ኛው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጉባኤ ለሦስት ቀናት ይቆያል።
የዜናው ምንጭ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ