ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት አካባበር አስመልክተው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትር በመግለጫቸው የዘንድሮ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ‹‹በጋራ እንገንባ›› በሚል መሪ ሃሳብ፤

በኢትዮጵያ ስነምህዳሩን ይበልጥ ማስፋት በሚያስችሉ በፓናል ውይይቶች እና እሳቤውን ይበልጥ በሚያሰርጹ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል ብለዋል፡፡ መንግስት የኢንተርፕረነርሺፕ ስነምህዳር ለማስፋት ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ ስነምህዳሩን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ተቋም በማቋቋም ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚያስችል አስተሳሰብ ለማስረጽ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርም የወለደው የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩቱ በአጭር ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የማሰልጠን እና እሳቤውን የማስረጽ አቅም መገንባቱን የገለጹት ክብርት ሚኒስትር ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጀምሮ ትልቅ ትኩረት ስለተሰጠው ባደገ እሳቤ እና በተደራጀ አቅም እየተመራ በየዓመቱ እድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ለኢንተርፕረነርሸፕ እና ኢኖቬሽን በሰጠችው ትኩረት እና ዘርፉን አስመልክቶ ባከናወነቻቸው ሁነቶች ብዛት በአፍሪካ 1ኛ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ ችላለች ብለዋል፡፡
የኢንተርፕረነር ስነምህዳር ለማስፋት እና እንደ ስርዓት ለመትከል መንግስት ለዘርፉ እድገት ጉልህ ፋይዳ የሚጫወተውን የስታርትአፕ አወጅን ጨምሮ የወጣት ኢንተርፕረነሮች ኢንቨስትመንት ባንክ እስከ ማቋቋም መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር የሚያዘጋጁት የአለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ከህዳር 8-18/2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ይፋዊ የመክፈቻ መርሃ ግብር የፊታችን ሰኞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ህዳር 6/2018 ዓ.ም ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊ ትኩስ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
Official Website: mols.gov.et
Facebook: https://web.facebook.com/MolsFDRE
Telegram: t.me/fdre_mols
TikTok: tiktok.com/@mols_official
Twitter / X: twitter.com/Jobs_ሚኒስቴር
WhatsApp: whatsapp.com/channel/0029VakCgcYIyPtTbPZtDW1y