ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ማ ታህሳስ 17/ 2012 ዓ.ም
የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል የስልጠና ሁኔታን በሚመለከት የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት ታህሳስ 16/2012 ዓ.ም በገነት ሆቴል ውይይት ተደርጓል፡፡ የአካዳሚክ ስራዎችን የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ግሩም ግርማ የተቋሙ የስልጠና ተደራሽነት ማደጉ፣ የሶፍትዌር ብልሽት መስተካከሉ፣ ሃምሳ ስምንት የስልጠና ሞጁሎች መዘጋጀታቸው፣ ቀርቶ የነበረው የዲግሪ መርሐ ግብር መጀመሩና የጥናትና ምርምር ስራዎች ከባለፈው የተሻለ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ዳንኤል በቀለ የአስተዳደርና ልማት ዲን በበኩላቸው አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በወቅቱ ግዥ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል ለሃምሳ ዓመታት በዘርፉ ላይ ትኩረቱን በማድረግ የስልጠና፣ የማማከርና የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ብቸኛ የመንግስት ተቋም ሆኖ ሳለ የተቋሙን አቅም በማሳደግ በዲግሪና ከዚያ በላይ በሆነ የትምህርት ደረጃ ለማስተማር ተቋሙን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ለማሳደግ በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከተው አካል ቢቀርብም ሳይጸድቅ በመቆየቱ በስልጠና ሂደቱ ላይ ተጽኖ እየፈጠረ መሆኑ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
ለሰልጣኞች የመኝታና የምገባ ስርዓቶች ባለመኖሩ የሚሰጣቸው 510 ብር የኪስ ገንዘብን ተጠቅመው ስልጠናቸውን ለመከታተል አስቸጋሪ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ደምቡ እንዲጸድቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም የሚመለከተው አካል ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው በ2012 ትምህርት ዓመት የተሻለ የስልጠና ጥራት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡