ሆ.ቱ.ሥ.ማ.ማ ሰኔ 25/2013 ዓ.ም የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል በ2013 አፈጻጸምና የ2014 ዕቅድ ላይ ከማኔጅመንት አባላት ጋር በነበረው ውይይት ዕቅዱ በአብዛኛው መፈጸሙ ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ስራዎች በአብዛኛው በተሻለ ሁኔታ መከናወናቸውን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ገልጸዋል፡፡
በተለይም ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ከመወጣት አንጻር የተሰሩ ስራዎችን ያስታወሱ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖና የመፍትሔ አቅጣጫን አስመልክቶ በተቋሙ የተሰራው ጥናት የዘርፉን የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል ለማዘጋጀት ትልቅ ግብዓት እንደ ነበር አንስተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በተግባር የተደገፈና ጥራት ያለውን ስልጠና ለመስጠት የተሰሩ ስራዎችም በጎ እንደ ነበሩ ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ክፍተት የታየባቸው የስራ ክፍሎችና ቀጣይ መሻሻል ያለባቸው የአሰራር ሥርዓት ዙሪያ ዋና ዳይሬክተሯ አቅጣጫና ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በቀጣይ 2014 በጀት ዓመት ዕቅድና በዝግጅት ምዕራፍ የሚከናወኑ ስራዎች ተለይተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አዲስ ሰልጣኞች በክረምት ስልጠናቸውን የሚከታተሉ በመሆኑ ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና እንዲሰጥም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡