“ የሆቴል እና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት እና ማሰልጠኛ ማዕከላት ትኩረት ሰጥተው ከኢንዱስትሪው ጋር መሥራት አለባቸው ”
በከር ሻሌ (ዶ/ር)

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
በሆቴል እና ቱሪዝም ሙያ ስልጠና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል፡፡ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከጀርመን ልማት ትብብር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ውይይት በንግግር ያስጀመሩት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ በከር ሻሌ (ዶ/ር) በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ትብብርን አጠናክሮ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ምቹ ሥራ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት ሥርዓተ ስልጠናውን በጋራ በመቅረፅ ፣ በማሰልጠን እና በመመዘን ጭምር ከሆቴል እና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት እና ማሰልጠኛ ማዕከላት ጋር ትኩረት ሰጥተው በጋራ መሥራት አለባቸው በማለት የጀርመን መንግስት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እያደረገ ካለው ድጋፍ ባሻገር ይህንን ውይይት በማዘጋጀቱ አመስግነዋል፡፡
የጀርመን ትብብር ልማትን ወክለው ንግግር ያደረጉት ቤንጃሚን ሀከር ኢትዮጵያ በቱሪዝም ብዙ ሀብት ያላት በመሆኑ ዘርፉን በብቁ ባለሞያዎች በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል እና ለዚህም የጀርመን መንግስት ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ቱሪዝም ኢንስቲትዩት፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ሃያት ሪጀንሲ፣ ኩሪፍቱ ሪዞርት፣ ኢትዮጵያ ሼፍ ማህበር፣ ኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ሃሳባቸውን ሲያቀረቡ በዘርፉ ተባብሮ ለመሥራት አስቸጋሪ ነበሩ ያሏቸውን በስልጠና እና ገበያው መካከል ያሉ ክፍተቶችን እንዲሁም የማሰልጠኛ ተቋማትን አቅም እንደችግር ያነሱ ሲሆን በቀጣይም በጋራ መሥራቱ የሚጠቅመው ለጋራ በመሆኑ ተባብሮ በመሥራት የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
0 Comments
Write a comment…