ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት እና ለመደገፍ የሚያስችል አውደ ጥናት በአዳማ እያካሄደ ነው።

የማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት፤ በዘርፉ የሚታየው የሰው ሀይል አቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ችግር፣ በዘላቂነት ለመቅረፍ ሲባል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሀገራችን የዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል በስፋት አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የልህቀት ማዕከል ይሆናል ሲባል የላቀ ስልጠና፣ የላቀ የምርምር ሥራ እና የላቀ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል ማለት ነው፡፡
“ዛሬ እየተካሄደ የሚገኘው አውደ ጥናት በተለይ በገበታ ለሀገር እየተሰሩ በሚገኙ ሜጋ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚያተኩር ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራትና ዘርፉ የሚፈልገው በስነ ምግባርና በሙያ የዳበረ ባለሙያ ለማግኘት እንዲቻል አውደ ጥናቱ የራሱን ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢፌድሪ መንግስት ልማትን ለማፋጠን ከዚህ ቀደም ግብርና መርህ የሆነውን ፖሊሲውን በመቀየር የብዝሃ ዘርፍ መርህን እየተከተለ ነው። ከዚህ ውስጥ የቱሪዝ ዘርፍ አንዱ ነው።
በዚህ መነሻ የመዳረሻ ልማት ላይ በርካታ ስራዎችና ተግባራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
“የቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ባለሙያዎች ለማፍራት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል” ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፤ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ግቡን ለማሳካት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በዳግም ከበደ